የአውሮፓ ህብረት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቁጥጥር ህግን አጸደቀ
ህጉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት የሰው ልጆችን ደህንነት እና መብት እንዳይጋፋ የሚቆጣጠር ነው ተብሏል
በቴክኖሎጂው ጥቅማቸው የሚጎዳ አካላትም ክስ የሚያቀርቡበትን ሂደት አስቀምጧል
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ አጸደቁ።
የህብረቱ አባል ሀገራት ተደራዳሪዎች በብራሰልስ 36 ስአት የወሰደ ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፈጠራን በማይጎዳ መልኩ በአውሮፓ እንዴት ጥቅም ላይ ይዋል በሚለው ዙሪያ የመከሩት ተደራዳሪዎቹ፥ የዘርፉን መቇጣጠሪያ ህግ ማጽደቃቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
አውሮፓን በዘርፉ ህግ በማውጣት ቀዳሚ ያደረጋት ውሳኔ የአሜሪካውን ኦፕን አይ ኩባንያ ንብረት ቻትጂፒቲን ጨምሮ የተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተጠቃሚ ቴክኖሎጂዎች መቆጣጠር የሚያችስል ነው ተብሏል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የሚደረገውን ፉክክር ጤናማ ከማድረግ ባለፈ ተጠያቂነትንም ያስፈናል ብለዋል የአውሮፓ ህብረት የማርኬቲንግ ኮሚሽነር ቴሪ ብሪተን።
እንደቻትጂፒቲ ባሉ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎች መብታቸው የሚነካና ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ካሳ የሚጠይቁበትን አሰራርም በግልጽ ማስቀመጡ ነው የተነግረው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ላይን ህጉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት የሰው ልጆችን ደህንነት እና መብት እንዳይጋፋ ያግዛል ሲሉ አምካሽተውታል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ መተማመን ይፈጥራል የተባለው ህግ ላይ የህብረቱ ፓርላማ በቀጣይ አመት ድምጽ ይሰጥበታል።
“ታሪካዊ” ነው የተባለው የህብረቱ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቁጥጥር ህግ ከ2025 በፊት ተግባራዊ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ብሪታንያ፣ አሜሪካ እና ቻይናም ተመሳሳይ ህግ ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።