አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በ10 ዓመት ውስጥ ከሰው ልጅ የማሰብ አቅም በላይ እንደሚሆን ተገለጸ
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከወዲሁ ቁጥጥር እንዲደረግበት ባለሙያዎች በማሳሰብ ላይ ናቸው
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ህግ በማዘጋጀት ላይ ናቸው ተብሏል
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በ10 ዓመት ውስጥ ከሰው ልጅ የማሰብ አቅም በላይ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
የጃፓኑ ሶፍት ባንክ መስራች እና ስራ አስኪያጅ ማሳዮሺ ሰን እንዳሉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በቀርቡ ከሰው ልጆች የማሰብ አቅም በላይ ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ እድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በ10 ዓመታት ውስጥ የሰወ ልጆችን የማሰብ አቅም በ10 እጥፍ ሊበልጥ ይችላልም ብለዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ በቶኪዮ በተካሄደ የቴክኖሎጂ እና ቢዝነስ ጉባኤ ላይ እንዳሉት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ከሰው ልጆች የማሰብ አቅም በላይ ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ እድገት በዚሁ ከቀጠለ ትራንስፖርቴሽን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ የመድሃኒት ኩባንያዎችን እና ሌሎች ዘርፎችን እንደሚጎዳም ተገልጿል፡፡
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሰው ልጆች አደጋ ደቅኗል - መስክ
ይህ እንዳይሆን ደግሞ የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ቁጥጥር ስር መዋል አለበት የሚሉት ማሳዮሺ በተለይም ወጣቶች ለዚህ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ አክለውም ቀጣዩ ዓለም በአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ይሆናል ይህን ማድረግ የቻለ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ ይሆናልም ብለዋል፡፡
የቡድን ሰባት ሀገራት በጃፓኗ ሂሮሽማ ባደረጉት ጉባኤ የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ ጥብቅ ቁጥጥር ካልተደረገበት ለዓለም አስጊ እንደሚሆን መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ቴክኖሎጂው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን እና ሀላፊነት ባለው መንገድ መጠቀም የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም ተስማምተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት ላይ ሲሆኑ የዓለማችን ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በረቂቅ ህጉ ዙሪያ መወያየት ጀምረዋል ተብሏል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊትም የሜታ፣ ጎግል፣ ትዊተር (ኤክስ) እና መሰል ተጽዕኖ ፈጣሪ ኩባንያ ባለቤቶች በዋሸንግተን በአካል ተገናኝተው መክረውም ነበር፡፡