የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሰው ልጆች አደጋ ደቅኗል - መስክ
ቴክኖሎጂው በገለልተኛ አካል ቁጥጥር ካልተደረገበት በሰው ልጆች ህልውና ላይ አደጋ መጋረጡ አይቀርም ነው ያሉት የአለማችን ቀዳሚው ቢሊየነር
የአለማችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአሜሪካ ምክክር አድርገዋል
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአለማችን ላይ የደቀነውን አደጋ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጭምር መግለጽ ጀምረዋል።
የኤክስ ወይንም የቀድሞው ትዊተር ባለቤት ኤለን መስክ ቴክኖሎጂው በገለልተኛ አካል ቁጥጥር እስካልተደረገበት ድረስ የሚደቅነው አደጋ ከባድ መሆኑን መጠራጠር የለብንም ብለዋል።
“ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁሉንም የሰው ልጆች የማጥፋት እድሉ ከዜሮ ከፍ ያለ ነው” በማለትም ከዚህ ቀደም በባለሙያዎች ሲነሱ የቆዩ ስጋቶችን ተጋርተዋል።
የአለማችን ቀዳሚው ቢሊየነር ኤለን መስክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ጥብቅ እና ቅድመ ክትትል የሚያደርግ ገለልተኛ ተቋም ሊኖር ይገባል የሚለውን አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ሴናተሮች መግለጻቸውንም ኤንቢሲ ዘግቧል።
ኤለን መስክን ጨምሮ የማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ እንዲሁም የሜታው ማርክ ዙከርበርግ ትናንት በካፒቶል ሂል በተካሄደ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጉባኤ ተሳትፈዋል።
ለሶስት ሰአታት የተደረገው ምክክር የአለማችን ፈተናም እድልም ሆኗል የተባለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ በቀጣይ ምን ይደረግ የሚል ይዘት ያለው ነበር።
ከስብሰባው በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት ኤለን መስክ “ሁሉም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲያድግ ይፈልጋሉ፤ በቴክኖሎጂው ወደ ኋላ መቅረት የሚያደርሰውን ጉዳትም ያውቁታል፤ ችግሩ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን መቀነሱ ላይ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ቴክኖሎጂው በየትኛውም አለም የሚገኝ የሰው ልጅን አደጋ ላይ ሊጥል መቻሉንም መዘንጋት የለብንም ነው ያሉት።
የአሜሪካ መንግስት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመቆጣጠር ያግዛል ያለውን ፖሊሲ ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ጋር መክሮበታል።
ስብሰባውን የመሩት የዴሞክራት ሴናተሩ ቹክ ስቹመር ጉባኤውን “ታሪካዊ” ነው ቢሉትም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ስራ አስፈጻሚዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመቆጣጠር ምን አይነት እርምጃ ይወሰድ በሚለው ዙሪያ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን አብራርተዋል።
የኦፕንኤአይ ኩባንያ ባለፈው አመት ያስተዋወቀው ቻትጂፒቲ ለየትኛውም ጥያቄ ምላሽ የመስጠትና የተለያዩ ጽሁፎችንም የማዘጋጀት አገልግሎት ጀምሯል።
ይሁ እንጂ ቴክኖሎጂው የሚሰጣቸው መልሶች ስህተት አላቸው፤ የሌሎችን የፈጠራ ውጤቶች በመቀማት የባለቤቶችን ዋጋ ያሳጣል የሚሉና ሌሎች ትችቶች ሲነሱ ቆይተዋል።
ቴክኖሎጂው በተለይ የቢሮ ስራዎችን እንደሚቀማ የሚያመላክቱ በርካታ ጥናቶች መውጣታቸውም ይታወሳል።