በኮፕ28 የግብርና ዘርፉን ለማዘመን 17 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ስምምነት ተደርሷል
አረብ ኤምሬትስና አሜሪካ የሚመሩት “ኤም ፎር ክላይሜት” ኢኒሼቲቭ በግብርና ማዘመን ላይ የሚውለው መዋዕለ ንዋይ በእጥፍ እንዲያድግ ወስኗል
ከ600 በላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለኢኒሼቲቩ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል
የግብርናው ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እንዲሆንና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ 17 ቢሊየን ዶላር መመደቡ ተነገረ።
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ነው ስምምነት የተደረሰው።
አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ የሚመሩት “ኤም ፎር ክላይሜት” ኢኒሼቲቭ የግብርውን ዘርፍ ለማዘመን እየሰራ ይገኛል።
ኢኒሼቲቩ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ባለፈው አመት በተካሄደው የኮፕ27 ጉባኤም የግብርናውን ዘርፍ በቲክኖሎጂ እና ፈጠራ ስራዎች ለማገዝ የ8 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት መጀመሩ ይታወሳል።
በኮፕ28 ጉባኤም ይህን ኢንቨስትመንት በእጥፍ አሳድጎ 17 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ከስምምነት ተደርሷል።
ከ600 በላይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኢኒሼቲቩን ለመደገፍም ስምምነት መፈራረማቸው ነው የተገለጸው።
ከኢንቨስትመንቱ ውስጥ 12 ቢሊየን ዶላሩ በአረብ ኤምሬትስ፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያና ካናዳን ጨምሮ ከ30 በላይ ሀገራት የመንግስት አጋር ድርጅቶች፤ ቀሪው 5 ቢሊየን ዶላር ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ይሸፈናል ተብሏል።
የግብርናው ዘርፍ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተኑ ከሚገኙት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ፈጠራዎችን የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርገው “ኤም ፎር ክላይሜት” ኢኒሼቲቭም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል።