140 ሀገራት የተፈራረሙት “የግብርና፣ ምግብ ስርአትና የአየር ንብረት ለውጥ” ዲክላሬሽን
ኮፕ28 በምግብ ስርአትና በግብርና ላይ ያተኮረ ዲክላሬሽን የተፈረመበት የመጀመሪያው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሆኗል
ፈራሚዎቹ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገት የሚውል 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል
በሰው ልጆች ጤና እና ህልውና ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ግብርናው በግንባር ቀደምነት ይነሳል።
ግብርና እና የምግብ ማምረት ሂደት በራሱ ለከባቢ አየር መዛባት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው የሚነገረው።
የቢሊየኖችን የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ የጣለው ቀውስ በየጊዜው አሳሳቢነቱ ጨምሯል።
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ በዱባይ ሲካሄድም በአየር ንብረት ለውጥ፣ ግብርና እና ምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ የስምምነት መግለጫ (ዲክላሬሽን) ተፈርሟል።
ዲክላሬሽኑን የፈረሙት 140 ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና እና ምግብ ስርአት ላይ የሚያስከትለውን ፈተና በጋራ ለመቀነስ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
የኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂዮ ሜሎኒ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊከን የመሩትና በግብርና እና ምግብ ስርአቱ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን የዳሰሰ ውይይት ተካሂዷል።
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ለረሃብ የሚያጋልጣቸውን ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱና አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።
ብራዚል፣ ቻይና እና አሜሪካን ጨምሮ 140ዎቹ የዲክላሬሽኑ ፈራሚ ሀገራት በድምሩ 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ህዝብ ይኖርባቸዋል።
ከአለም የምግብ ምርት 70 በመቶውን የሚሸፍኑት እነዚህ ሀገራት ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀው በካይ ጋዝ ሩቡን ያዋጣሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና እና የምግብ ስርአቱ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ዘርፉ የሚያስከትለው ብክለትም ሊጤን እንደሚገባ የተነሳበት የኮፕ28 ጉባኤ፥ የምግብ ዋስትናቸው በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ ለወደቀ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግም ስምምነት ተደርሶበታል።