አየር ላይ የተናጠው የስፔን አውሮፕላን 30 ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ
325 ሰዎችን አሳፍሮ ከማድሪድ ወደ ኡራጓይ መዲና ሞንትቪዲዮ እያመራ የነበረው የኤር ዩሮፓ አውሮፕላን በብራዚል ለማረፍ ተገዷል
የሲንጋፖር አየር መንገድም ከሳምንታት በፊት ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል
አየር ላይ “በጠንካራ ነውጥ” በተመታው የኤር ዩሮፓ አውሮፕላን 30 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።
መነሻውን ከስፔን መዲና ማድሪድ አድርጎ ወደ ኡራጓይ ዋና ከተማ ሞንትቪዲዮ እያመራ የነበረው ቦይንግ 787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላን አየር ላይ መንገደኞችን ንጧል።
የበረራ ቁጥሩ “UX045” የሆነው አውሮፕላን መንቀጥቀጥ የመቀመጫ ቀበቶ ያላደረጉ መንገደኞችን ከአውሮፕላኑ ጣሪያ ጋር አላትሞ ጉዳት ማድረሱንም የስፔኑ ኤር ዩሮፓ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በዚህም ከመዳረሻው ሞንትቪዲዮ ሳይደርስ በሰሜን ምስራቅ ብራዚል በሚገኘው ናታል በተሰኘ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ መገደዱም ነው የተገለጸው።
ጉዳት የደረሰባቸው የተለያየ ሀገር ዜግነት ያላቸው መንገደኞችም ወደ ሆስፒታሎች ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል መባሉን ሬውተርስ ዘግቧል።
የኤር ዩሮፓ አደጋ የተሰማው በሲንጋፖር አየርመንገድ አውሮፕላን ላይ ተመሳሳይ ችግር ከገጠመ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ከለንደን የተነሳውና መዳረሻውን ሲንጋፖር ያደረገው ቦይንግ 777 አውሮፕላን በባንኮክ በድንገት ለማረፍ መገደዱና የ1 ሰው ህይወት አልፎ በ30 መንገደኞች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
በአየር ጸባይ እና ሌሎች ምክንያቶች በበረራ ወቅት ከአውሮፕላኖች መንገራገጭ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎች በአየር ትራንስፖርት ላይ ደጋግመው ይታያሉ።
ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2018 ድረስ ባሉ አመታት ውስጥ ከተመዘገቡ የአውሮፕላን አደጋዎች ውስጥ ሲሶው በአውሮፕላኖች የጉዞ መረበሽ ወይም መናጥ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ይላል የአሜሪካ ብሄራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ።
ክስተቶቹ መንገደኞችን ለጉዳት ቢዳርጉም በአውሮፕላኖች ላይ ምንም ችግር እንዳልፈጠሩም በማከል።
በመሆኑም መንገደኞች በበረራ ወቅት የመቀመጫቸውን ቀበቶ እንዲያስሩ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች የሚተላለፉት ለዚህ መሆኑንም አውስቷል።