የሲንጋፖር አየርመንገድ በተናጠው አውሮፕላን ለተሳፈሩ መንገደኞች ካሳ ሊከፍል ነው
አየርመንገዱ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው 25 ሺህ፤ መጠነኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ደግሞ 10 ሺህ ዶላር እንደሚከፍል አስታውቋል
ከለንደን ወደ ሲንጋፖር ሲበር የነበረው አውሮፕላን በገጠመው ችግር 1 መንገደኛ ህይወቱ ማለፉና ከ30 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል
የሲንጋፖር አየርመንገድ ባለፈው ወር በበረራ ወቅት በተናጠው አውሮፕላን ለተሳፈሩ መንገደኞች ካሳ ሊከፍል ነው።
ከለንደን ወደ ሲንጋፖር ሲበር በነበረው አውሮፕላን ተሳፍረው መጠነኛ ጉዳት ለደረሰባቸው መንገደኞች 10 ሺህ ዶላር እንደሚከፍል አየርመንገዱ አስታውቋል።
የአውሮፕላኑ መናወጥ ከባድ ጉዳት ያደረሰባቸውና በሆስፒታሎች ቀጣይ ክትትል ለሚፈልጉ መንገደኞች ደግሞ 25 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል ብሏል አየርመንገዱ።
የበረራ ቁጥሩ “ኤስኪው321” የሆነው አውሮፕላን ከለንደን ከተነሳ ከ11 ስአት በኋላ ሲበርበት ከነበረው 37 ሺህ ጫማ ከፍታ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ወደ 31 ሺህ ጫማ መውረዱ ቀበቶ ያላሰሩ መንገደኞችን ከእቃ መጫኛው ጋር አጋጭቶ ወደ ወለሉ ወርውሯቸዋል መባሉ ይታወሳል።
በዚህም የ73 አመት መንገደኛ ህይወት ማለፉና ከ30 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው መገለጹ አይዘነጋም።
አውሮፕላኑ በተፈጠረው አደጋ ምክንያት በድንገት ባረፈባት የታይላንዷ ባንኮክ ከተማ እስከባለፈው ሳምንት ድረስ 20 መንገደኞች ከሆስፒታል አልወጡም።
አብዛኞቹም የጀርባ አጥንት መሰበርና የጭንቅላት ጉዳት እንደገጠማቸው የባንኮክ ሆስፒታል አስታውቋል።
የሲንጋፖር አየርመንገድ ሁሉም መንገደኞች የከፈሉት ሂሳብ ተመላሽ ተደርጎ ለደረሰባቸው መጉላላትም ይካሳሉ ብሏል።
211 መንገደኞች እና 18 የበረራ ቡድን አባላትን ያሳፈረው አውሮፕላን ግንቦት 20 2024 ላይ ያጋጠመው ችግር ከአየር ጸባይ ጋር የተገናኘ መሆኑን የሲንጋፖር ትራንስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በአየር ጸባይ እና ሌሎች ምክንያቶች በበረራ ወቅት ከአውሮፕላኖች መንገራገጭ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎች በአየር ትራንስፖርት ላይ ደጋግመው ይታያሉ።
ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2018 ድረስ ባሉ አመታት ውስጥ ከተመዘገቡ የአውሮፕላን አደጋዎች ውስጥ ሲሶው በአውሮፕላኖች የጉዞ መረበሽ ወይም መናጥ ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው ይላል የአሜሪካ ብሄራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ።