የፈረንሳይ አየር መንገድ በፓሪስ ኦሎምፒክ ምክንያት እስከ 180 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችል ገለጸ
አየር መንገዱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳታፊዎችን በማጓጓዝ ገቢ የማግኘት እቅድ አውጥቶ ነበር
በቀን 125 ሺህ መንገደኞችን ለማጓጓዝ እቅድ የነበረው የፈረንሳይ አየር መንገድ የኦሎምፒክ ተሳታፊዎች ሌላ ምርጫ እየተከተሉ ነው ብሏል
የፈረንሳይ አየር መንገድ በፓሪስ ኦሎምፒክ ምክንያት እስከ 180 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችል ገለጸ።
በየ አራት አመቱ የሚካሄደው ተወዳጁ የኦሎምፒክ ስፖርት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አስተናጋጅነት ከቀናት በኋላ ይካሄዳል።
ኤር ፍራንስ የተሰኘው የፈረንሳይ አየር መንገድ ይህን የፓሪስ ኦሎምፒክ ታሳቢ በማድረግ እስከ 180 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ሊያገኝ እንደሚችል እቅድ አውጥቶ ነበር።
ይሁንና አየር መንገዱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለመሳተፍ የሚጓዙ መንገደኞች ሌላ ምርጫ እየተከተሉብኝ ነው ሲል አስታውቋል።
ዩሮ ኒውስ ኤር ፍራንስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ውድድሩን ለመካፈል ወደ ፓሪስ ከሚመጡ አጠቃላይ አትሌቶች እና ተመልካቾች ውስጥ 20 በመቶውን ለማጓጓዝ እቅድ ነበረው።
በቀን 125 ሺህ መንገደኞችን በማጓጓዝ እስከ 180 ሺህ ዩሮ ገቢ ለማግኘት እቅድ ቢኖረንም መንገደኞች እስካሁን የቅድመ በረራ እቅዳቸው ላይ አልተመዘገቡም ብሏል።
ከዚህ ባለፈም አትሌቶች እና ተመልካቾች ከኤር ፍራንስ ይልቅ ሌሎች አየር መንገዶችን እና የመጓጓዣ አማራጮን ለመጠቀም እያሰቡ ነውም ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
በፈረንሳይ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት እና የአደባባይ ተቃውሞዎች ወደ ፓሪስ ለመምጣት ፍላጎት የነበራቸውን ጎብኚዎች ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ትልቁ ምክንያት እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ፓሪስ ከተማ የዘንድሮውን ኦሎምፒክ ውድድር ከሀምሌ 19 እስከ ነሀሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የምታስተናግድ ሲሆን ከተማዋ የኦሎምፒክ ውድድርን ስታስተናግ ከ100 ዓመት በኋላ ነው።