ፈረንሳይ በጨዋታ ምንም አይነት ጎል ሳታስቆጥር ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለች በታሪክ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች
በፖርቹጋል እና ስሎቫኒያ መካከል የተደረገው በድራማ የተሞላ ጨዋታ በመለያ ምት ተጠናቋል
በአውሮፓ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ውድድር ፖርቹጋል እና ፈረንሳይ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀላቸውን አረጋገጡ
17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ ትናነት ምሽት ላይ ቀጥሎ ሲደረግ ፈረንሳይ እና ፖርቹጋል ወደ ሩብ ፍጻሜው መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
በፖርቹጋል እና በስሎቫኒያ መካከል የተደረገው ድራማ የተሞላበት ጨዋታ የስፖርቱን ቤተሰብ ትኩረት የሳበ ትንቅንቅ የተደረገበት ነበር።
ስሎቫኒያዎች ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው በቀረቡብት የምሽቱ ጨዋታ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ ምንም ጎል ባለመቆጠሩ ሁለቱ ቡድኖች ወደ ተጨማሪ 30 ደቂቃ አምርተዋል።
በጭማሪ ሰአት ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በጨዋታው ያገኝውን ፍጹም ቅጣት ምት ሳይጠቀምበት በመቅረቱ በእንባ ሲታጠብ ታይቷል።
የ39 አመቱ የእግር ኳስ ጠቢበኛ ለሀገሩ የሚያደርገው የመጨረሻ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር በዋንጫ እንዲታጀብ ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ባባከነው አድል በእጅጉ አዝኖ ታይቷል።
ጭማሪ 30 ደቂቃዎችን አጠናቆ ወደ መለያ ምት ያመራው ጨዋታ የፖርችጋሉ ግብ ጠባቂ ዲያጎ ኮስታ ሶስት መለያ ምቶችን በማዳን ለሀገሩ አይረሴውን ውለታ ውሏል። በዚህም 3ለ0 በሆነ ውጤት ፖርቹጋል ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
ክርስቲያኖ በሀዘን እና በደስታ መካከል የታየበት የምሽቱ ጨዋታ ፖርቹጋልን በውድድሩ ተጨማሪ እድልን ሰጥቷል። በአውሮፓ ዋንጫ የምንግዜም ከፍተኛ ገብ አስቆጣሪው ሮናልዶ ከጨዋታው በኋላ ፍጹም ቅጣቱን በመሳቱ የሀገሩን ልጆች እና ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠይቋል።
በምሽቱ ሌላኛው ጨዋታ በፊፋ የደረጃ ዝርዝር ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚገኙት ፈረንሳይ እና ቤልጂየምን አገናኝቷል።
ምሽት አንድ ሰአት ላይ የተደረገው ጨዋታ እስከ 84ተኛው ደቂቃ ድረስ ያለምንም ግብ ተጉዞ የቤልጅየሙ ቨርቶንገን በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ጎል ፈረንሳይ አሸናፊ ሆና መውጣት ችላለች።
በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችላ የነበረችው ቤልጅየም እድሎችን ወደ ውጤት መቀየር ሳትችል በመቅረቷ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች።
እድለኛው ብሄራዊ ቡድን የተባሉት ፈረንሳዮች በበኩላቸው በዘንድሮው ውድድር ለዋንጫ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል እንዱ ቢሆኑም በውድድሩ እያሳዩት የሚገኝው አቋም የተጠበቁትን ያህል አይደለም።
በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በጨዋታ ምንም ጎል ሳያስቆጥር ሩብ ፍጻሜን በመቀላቀል ስሙን ያስመዘገበው ብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለቱ ተቃራኒ ቡድኖች በራሳቸው ላይ ያስቆጠሩት ሲሆን አንዱ ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት የተገኝ ነው።
የጥሎ ማለፉ ውድድር ዛሬ ምሽት የሚጠናቀቅ ሲሆን ምሽት 1 ሰአት ላይ ሮማንያ ከ ኔዘርላንድ 4 ሰአት ላይ ደግሞ ኦስትሪያ ከ ቱርክ ይጫወታሉ።
የእንግሊዙ ዘሰን ጋዜጣ የጥሎ ማለፉ ውድድር በተጀመረበት ወቅት ባወጣው ጽሁፍ የዘንድሮውን ውድድር ተጠባቂ የሚያደርገው ከጥሎ ማለፉ ይልቅ በሩብ ፍጻሜ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው ብሎ ነበር።
ጋዜጣው እንዳስነበበው በውድድሩ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው እንግሊዝ ፣ ጀርመን ፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ጥሎ ማለፉን የሚሻገሩ ከሆነ በሩብ ፍጻሜው የሚኖራቸው ትንቅንቅ ይጠበቃል ብሏል።
ለአብነት ብሎ ካነሳቸው ጨዋታዎች መከከል ስፔን እና ጀርመን ወደ ጥሎ ማለፉ ከተሸጋገሩ የሚኖረውን ፍልሚያ በቀዳሚነት ጠቅሶታል።
አሁን ሁለቱ ቡድኖች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በመጪው አርብ ይፋለማሉ፡፡ በተመሳሳይ ቀን ምሽት 4 ሰአት ላይ ደግሞ ፈረንሳይ እና ፖርቹጋል የሚጫወቱ ይሆናል።