ቦይንግ-777 አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ታዘዘ
በዚህም በመላው ዓለም የሚገኙ 120 አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጭ ይሆናሉ ተብሏል
ይህ የታዘዘው ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን ከሰሞኑ ከገጠመው የሞተር ቃጠሎ ችግር ጋር በተያያዘ ነው
አየር መንገዶች ቦይንግ 777 አውሮፕላኖችን በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጭ እንዲያደርጉ አሜሪካዊው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ አዘዘ፡፡
ቦይንግ ይህን ያዘዘው ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን ከሰሞኑ ከገጠመው የሞተር ቃጠሎ ችግር ጋር በተያያዘ ነው፡፡
በዚህም በመላው ዓለም የሚገኙና ተመሳሳይ ሞተር ያላቸው 120 አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ አዟል ቦይንግ፡፡
አውሮፕላኖቹን የሚጠቀሙ አየር መንገዶች ችግሩ ተመርምሮ እስከሚታወቅ ድረስ ከአገልግሎት ውጭ እንዲያደርጉም መክሯል እንደ ዘ ጋርዲያን ዘገባ፡፡
ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ይህን ያደረገው የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በአውሮፕላኖቹ ላይ አስቸኳይ ወይም የተጠናከረ ፍተሻ እንዲደረግ በማዘዙ ነው፡፡
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከአሜሪካ ዴንቨር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ሃዋይ ሆኖሉሉ ይበር የነበረው ቦይንግ 777-200 አውሮፕላን በረራ በጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በአንደኛው ክንፉ የሞተር ችግር ገጥሞታል፡፡
ሞተሩ በእሳት ተያይዞ የአውሮፕላኑ አካል ክፍሎች ወደ መሬት ሲወድቁም ነበረ፡፡
ሆኖም በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩትን 231 መንገደኞች እና 10 የበረራ ቡድን አባላት ጨምሮ አካል ክፍሉ ሲወድቅ በነበረበት አካባቢ የደረሰ ሰብዓዊ ጉዳት የለም፡፡
24 የቦይንግ 777 አውሮፕላኖቹን በጊዜያዊነት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉንም አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡
የጃፓን አየር መንገድ እና ኦል ኒፖን ኤርዌይስም ለጊዜው በአውሮፕላኖቹ እንዳይገለገሉ በሃገሪቱ የአቪዬሽን ባለስልጣን ታዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለ ሁኔታው ያለው ነገር የለም፡፡
777-200 እና 777-300 አውሮፕላኖች በድሮ ሞዴልነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ነዳጅ አጠቃቀም ላይ ውጤታማ አይደሉምም ነው የሚባለው፡፡ ብዙዎቹ አየር መንገዶች እየተዋቸው እንደሆነም ይነገራል፡፡
ቦይንግ ከአሁን ቀደምም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዥያው ላየን ኤር ከደረሱ እጅግ አስከፊ አደጋዎች ጋር በተያያዘ የማክስ-8 አውሮፕላኖቹን ከበረራ ውጭ ለማድረግ ተገዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡