አሜሪካ በባይደን የመኖሪያ አካባቢ ምንም ዓይነት በረራዎች እንዳይደረጉ ከለከለች
እስካሁን ባለው የቆጠራ ውጤት ባይደን በ264 የውክልና ድምጽ እየመሩ ነው
ባይደን ምርጫውን ለማሸነፍ መቃረባቸውን ተከትሎ ተጨማሪ የደህንነት ሰዎች ወደ ዴሞክራቱ እጩ የመኖሪያ አካባቢ አቅንተዋል
አሜሪካ በባይደን የመኖሪያ አካባቢ ምንም ዓይነት በረራዎች እንዳይደረጉ ከለከለች
የአሜሪካ ብሄራዊ የአየር መከላከያ ደላዌር ዊልሚንግተን በሚገኘው የዴሞክራቱ እጩ ፕሬዝዳንታዊ ተወዳዳሪ ጆ ባይደን የመኖሪያ አካባቢ ምንም ዓይነት በረራዎች እንዳይደረጉ ከለከለ፡፡
የሃገሪቱ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ነበር ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ማግስት በረራውን በጊዜያዊነት የከለከለው፡፡
አብራሪዎች እንዲያውቁት የተደረገው ይህ ክልከላ ከእጩ ተወዳዳሪው መኖሪያ አንድ ማይል ራዲየስ ርቀት ውስጥ እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ ምንም ዓይነት በረራ ማድረግ እንደማይቻል ያትታል፡፡
በቅርብ ርቀት በሚገኘው የቤት ውስጥ የቼዝ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አቅራቢያ ጭምር መብረር እንደማይቻልም አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ማዘውተሪያ ስፍራው ምናልባትም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ትልቅ ቅድመ ግምትን ያገኙት ባይደን ማሸነፋቸውን አስመልክቶ ንግግር የሚያደርጉበት ሊሆን እንደሚችል ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
የባይደንን ተጠባቂ ድል ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ የደህንነት ሰዎች ወደ ደላዌር እንዳቀኑም ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡
እስከ አሁን ይፋ በተደረገ ውጤት ጆ ባይደን 20 ወካይ ድምጽ ያለውን የፔንሲልቫኒያ ግዛት መሪነት ከ ዶናልድ ትራምፕ ተረክበዋል፡፡ ከ98 በመቶ በላይ የድምጽ ቆጠራው ተጠናቆ ባይደን የፔንሲልቫኒያውን ፉክክር መምራታቸውን አጠናክረዋል፡፡
ቆጠራው ሊጠናቀቅ ከ4 ሺ ያነሰ ድምጽ በቀረው ጆርጂያም እየመሩ ይገኛሉ፡፡
በእስካሁኑ ውጤት ትራምፕ የኋይት ሀውስን ቁልፍ ለማስረከብ የተቃረቡ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ፕሬዝዳንቱ በተሸነፉባቸው አንዳንድ ግዛቶች ዳግም ቆጠራ እንዲካሔድ ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
ይህ የትራምፕ እንቅስቃሴ በብዙዎች ትችት ያስከተለባቸው ሲሆን የባይደን ቡድን የሕግ አካላትም ክስ ከተሰነዘረ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ትራምፕ በአሁኑ ወቅት በመምራት ላይ የሚገኙት 15 የውክልና ድምጽ ባለው ሰሜን ካሮላይና እና 3 ድምጽ ብቻ ባለው አላስካ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ምርጫውን ለማሸነፍ ውጤታቸው ይፋ ካልሆኑት 5 ግዛቶች ቢያንስ የአራቱን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡