ትራምፕ ሲመሩ የነበረው የጆርጂያ ግዛት ፊቱን ወደ ባይደን አዙሯል
ፌስቡክ በቀሪ ግዛቶች እንደሚያሸንፍ የሚገመተውን ዕጩ በመለጠፍ ለትራምፕ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል
በውጤቱ ወሳኝ ግዛቶች ፉክክሩ የቀጠለ ሲሆን ባይደን ምርጫውን ለማሸነፍ የተሻለ ዕድል አላቸው
በውጤቱ ወሳኝ ግዛቶች ፉክክሩ የቀጠለ ሲሆን ባይደን ምርጫውን ለማሸነፍ የተሻለ ዕድል አላቸው
በጉጉት እየተጠበቀ በሚገኘው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ወደ መጨረሻው በመቃረብ ላይ ነው፡፡
ምርጫው ከተካሔደ ከ 3 ቀናት በኋላ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መካከል ከፍተኛ ፉክክር እየተደረገባቸው ከሚገኙት ወሳኝ ግዛቶች መካከል በጆርጂያ እና ፔንሲልቫኒያ ልዩነቱ እጅግ እየጠበበ በመምጣት ላይ ነው፡፡
የዴሞክራቲክ ዕጩው ጆ ባይደን ፣ ትራምፕ በጥቂት ልዩነት ሲመሩ በነበረው ጆርጆያ ግዛት መሪነቱን ተረክበዋል፡፡ 16 ወካይ ድምጽ ባለው ጆርጂያ ቀሪ ያልተቆጠረ 9,000 ያህል ድምጽ ያለ ሲሆን እስካሁን ተቆጥሮ ይፋ በተደረገው ባይደን በ 917 ድምጽ መምራት ጀምረዋል፡፡
እስካሁን 264 ወካይ ድምጽ ማግኘታቸውን ያረጋገጡት ባይደን ለማሸነፍ 6 ድምጽ ብቻ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ለማሳካት ቀድሞውንም በመምራት ላይ የሚገኙበትን የኔቫዳን ውክልና ማግኘት ብቻይ ጠበቅባቸዋል፡፡ በ214 ድምጽ የሚከተሉት ትራምፕ በአንጻሩ ኔቫዳን ጨምሮ በተቀሩት 4 ግዛቶች ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሀሳብ ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ በሰሜን ካሮላይና ከፍ ባለ ድምጽ እየመሩ ይገኛሉ፡፡
ዘግይተው መጨረሻ ላይ እየተቆጠሩ የሚገኙት በፖስታ የተሰጡ ድምጾች በአብዛኛው ለባይደን የተሰጡ ናቸው፡፡
እስካሁን በአሜሪካ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታሪክ በመራጮቻቸውች ብዛት ሪከርድ መስበር የቻሉት ባይደን "ምርጫውን እንደማሸንፍ ጥርጥር የለኝም" ሲሉ ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ያለው ሁነኔታም ድል ወደ እርሳቸው ማጋደሉን የሚያመለክት ነው፡፡
ጆ ባይደን ምሽት በደላዋሬ ባደርጉት ንግግር "እስካሁን ነገሮች ያሉበት ሁኔታ በጣም ጥሩ እንደሆነ ይሰማናል፤ ቆጠራው ሲጠናቀቅ እኔና ካማላ ሀሪስ (ምክትላቸው) አሸናፊነታችን ይፋ እንደሚደረግ አልጠራጠርም" ብለዋል።
አሜሪካውያን የመጨረሻውን ውጤት ተረጋግተው እንዲጠብቁም ጠይቀዋል።
የትራምፕ ደጋፊዎች ቆጠራው እንዲቋረጥ የባየይደን ደጋፊዎች ደግሞ ሁሉም ድምጽ እንዲቆጠር በመጠየቅ በበርካታ ከተሞች ሰልፍ ወጥተዋል።
ትራመፕ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ደጋግመው ሲሉ እንደነበረው ምርጫው ስለመጭበርበሩ ገልጸው ቆጠራው እንዲቆም ጠይቀዋል። ይህም ትችትን አስከትሎባቸዋል። ይሁን እንጂ ቆጠራው የቀጠለ ሲሆን ትራምፕ በአንዳንድ ግዛቶች ክስ መክፈት ጀምረዋል፡፡
ትዊተር እና ፌስቡክ ትራምፕ ምርጫው ተጭብርብሯል እንዲሁም ምርጫውን አሸንፈናል በሚል የሚጽፏቸውን በርካታ ጽሁፎች እየተከታተሉ በመደበቅ እና በማስወገድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ዛሬ ደግሞ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ ፌስቡክ የፕሬዝዳንቱን ሀሰተኛ መረጃዎች ለማጋለጥ ከታማኝ ሚዲያዎች የሚያገኛቸውን የየግዛቱን ተገማች አሸናፊዎች በገጹ እንደሚለጥፍ አስታውቋል፡፡
በየግዛቱ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ወቅታዊ መረጃዎችን በመልቀቅ ለትራምፕ ያልተረጋገጡ ውንጀላዎች ምላሽ ለመስጠት ማሰቡን ነው ኩባንያው ይፋ ያደረገው፡፡
ምናልባትም የምርጫው አሸናፊ ዛሬ ሊታወቅ እንደሚችል በመዘገብ ላይ ነው፡፡