“ሕወሓት በፌዴራል ፖሊስ ሃይል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር ባለፈ ከፍተኛ የንብረት ዝርፊያ ፈጽሟል” የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
ከኦነግ/ሸኔ ታጣቂ ሃይል ጋር በመቀናጀት ከውጭ እና ከሃገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ላለፉት 2 ዓመታት ሃገሪቷን ሲያተራምሱ ስለመቆየታቸውም ነው የተገለጸው
ቡድኑ በትላልቅ የሃገሪቱ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ኃይል እንዳሰማራ መረጋገጡንም ኮሚሽኑ አስታውቋል
“ሕወሓት በትግራይ ክልል ተሰማርቶ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ሃይል ላይ ጭምር ጥቃት ከመሰንዘር ባለፈ ከፍተኛ የንብረት ዝርፊያ ፈጽሟል”-የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
ከሰሞነኛ ሃገራዊ የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው እና የኮማንድ ፖስት ፕሬስ ሴክሬተሪያት አቶ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
መንግስት በሃገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሟል ባለው ሕወሓት ላይ እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች ያብራሩት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው “ጽንፈኛ”ያሉት የሕወሓት ኃይል ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ለመስራት ያለመፈለግ፣ ህገ ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሰራዊት ኃይል ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌዴራል መንግስቱን ህገ ወጥ ነው ብሎ ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨት ሌሎች ለጸጥታ ስጋት የሆኑ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡
ከኦነግ/ሸኔ ታጣቂ ሃይል ጋር በመቀናጀት በተደራጀ መንገድ ከውጭ እና ከሃገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የሃገሪቷን ክፍሎች ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
“በሁሉም አካባቢዎች ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች በአንድም በሌላ መንገድ ሲያደራጁ ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና መረጃዎቻችን በአግባቡ አረጋግጠዋል” ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ባለው ህገመንግስታዊ ተልዕኮ በሁሉም የሃሪቱ ክፍል ተሰማርቶ የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ የሚጠብቅ ኃይል ነው፡፡
በትግራይም በ22 ትልልቅ ተቋማት ውስጥ ስምሪት አድርጎ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው እንደ ኮሚሽነር ጄነራሉ ገለጻ፡፡
ሆኖም “ህዝቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ሃይል በመመደብ ጥቃት ሰንዝሮበታል ከነዚህ ተቋማትም ከፍተኛ የንብረት ዝርፊያ ፈጽሟል”፡፡
ሰራዊቱም ራሱን ለመከላከል አንዳንድ ስራዎችን ከመስራት በተጨማሪ ከትግራይ ህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን ተከላክሏል፡፡
እንደ ኮማንድ ፖስቱ ፕሬስ ሴክሬተሪያት አቶ ሬድዋን ሁሴን ገለጻ ሰራዊቱ የውጊያ ዓላማ ሳይኖረው ህብረተሰቡ የሚገለገልባቸውን የሲቪል ተቋማት ሲጠብቅ የነበረ ነው፡፡ ሆኖም ከጥቃት አላመለጠም፡፡
ፕሬስ ሴክሬተሪያቱ “የተጀመረው የጋራ ተቋማቶቻችንን በመጉዳትና በማፍረስ አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ትንኮሳ ነው” ያሉም ሲሆን መንግስት ህግ የማስከበር እና ህገ መንግስቱን የማጽናት ስራ እንዲሰራ የተገደደበት ሁኔታ ነው መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡
ፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን በትላልቅ የሃገሪቱ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ኃይል እንዳሰማራ መረጋገጡንም መግለጫውን ዋቢ አድርጎ የተሰራው የኢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡
ትናንት በትግራይ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈ መግለጫ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያብራሩት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ለመደምሰስ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን”ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡