“ወንጀለኞቹን ከተደበቁበት እናወጣለን”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ጥረት “በህወሓት ግትርነት” መክሸፉንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት
“መከላከያ እየወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣የተወሰነ እና ሊደረስበት የሚችል ዓላማን ያነገበ ነው”
“ወንጀለኞቹን ከተደበቁበት እናወጣለን”- ጠ/ሚ ዐቢይ
በሰሜን ኢትዮጵያ በመከላከያ ሰራዊት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣የተወሰነ እና ሊደረስበት የሚችል ዓላማን ያነገበ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ባሳለፈው ማክሰኞ ትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱ እየወሰደ ስላለው እርምጃ የሚገልጹ መረጃዎችን በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
ዘመቻው ህግና ስርአትን ለማስፈን እና ህገ መንግስታዊ ስርአትን ለማስከበር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢየሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት የማስጠበቅ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ከህወሓት አመራር ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና፣በእርቅና በውይይት ለመፍታት ወራትን የወሰደ ጥረት በትዕግስት ማድረጉን የገለጹም ሲሆን ጥረቱ በወንጀለኛው ህወሓት ግትርነት መክሸፉን አስታውቀዋል፡፡
ይባስ ብሎ በስተመጨረሻ በክልል ሰፍሮ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ነው የገለጹት፡፡
የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣናትንና ተግባራት የሚዘረዝረው የህገ መንግስቱ አንቀጽ (አንቀጽ 51) የፌዴራል መንግስቱ “ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል” በሚል እንደሚደነግግ በመጥቀስም ኢትዮጵያ ለወንጀለኛ አካላት ቦታ እንደሌላት አስፍረዋል።
መንግስት ይህንኑ ግዴታ ለመወጣት በሃገሪቱ ብሄራዊ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በፈጸመው ቡድን ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት፡፡
“ኩሩ ኢትዮጵያዊ የሆነው የትግራይ ህዝብ እና ሌሎች ዜጎች ለዘለዓለም ፍትህ ሊነጠቁ አይችሉም”ም ብለዋል።
“እነዚህን ወንጀለኛ አካላት ከተደበቁበት አውጥተን አገራችንን ለሁሉም በቂ ወደ ሆነው ዘላቂ የብልጽግና ጎዳና እንመልሳታለን”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት፡፡