የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ስድስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቀቀ
የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስድስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቀው የሙከራ ኃይል ለማመንጨት ዝግጁ መሆናቸውን የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ቀለሙ ገለፁ፡፡
ለሙከራ ለሚያስፈልጉ ተርባይኖች፤ የውስጥ ገመድ ዝርጋታ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑንም አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል፡፡
የሙከራ ሥራውን ለማከናወን በአሁኑ ሰዓት ቀሪ የማከፋፈያ ጣቢያ፣ የማስተላለፊያ መስመሮች፣ የታወር ተከላና ገመድ ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶት በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት፡፡
በኃይል ማመንጫው እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 48 ተርባይኖች የሚኖሩት ፕሮጀክቱ፤ የ34 ተርባይኖች ታወር የመሰረት ግንባታ ኮንክሪት ስራ ተከናውኗል፡፡
የቀሪ ተርባይኖች የታወር እና የቦክስ ትራንስፎርመር መሰረት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ፕሮጀክቱ፣ በስፍራው የከርሰ ምድር ውሃ ተቆፍሮ አለመገኘቱ፣ ባለፈው ክረምት በነበረው ከባድ ዝናብና ጎርፍ ምክንያት ስራው ተስተጓጉሎ መቆየቱና በደለል የተደፈኑ ጉድጓዶችን እንደገና ለመስራት መገደዱ እንዲሁም ኮንትራክተሩ ለሰራው የጠየቀውን ክፍያ አበዳሪው ባንክ በወቅቱ አለመክፈሉ በግንባታ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም የመርሃ ግብር ክለሳ በመሰራት ላይ ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 46 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል ተብቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በ700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሱማሌ ክልል አይሻ ደወሌ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለግንባታውም 15 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት ቀሪው 85 በመቶ ደግሞ በቻይና ኤግዚም ባንክ የሚሸፈን 257 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበለት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡