የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለጀነራል አልቡርሃን አቀባበል አድርገውላቸዋል
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጦርነት ሰባት ወራት አስቆጥሯል
የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ፕሬዝዳንትና የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጀነራል አልቡርሃን አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በተለያዩ ጉዳዮች መክረዋል።
ሰባተኛ ወሩን የያዘው የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጦርነት ከ9 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለው ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲቆም የሚደረገው ጥረትም ቀጥሏል።
ሁለቱ ሃይሎች በሪያድ በተደጋጋሚ ለድርድር ቢቀመጡም እስካሁን ከስምምነት ላይ አልደረሱም።
በአዲስ አበባም በቅርቡ በሱዳን የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ያለመና ከ80 በላይ የሀገሪቱ የፖለቲካና ሲቪል ድርጅቶች የተሳተፉበት ምክክር መደረጉ አይዘነጋም።
በካርቱም የሚገኘው ኤምባሲዋ በአየር የተደበደበባት ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር ሁለቱን ተፋላሚ ሃይሎች ለማቀራረብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
የሱዳን ጦር በሰኔ ወር በአዲስ አበባ በተካሄደውና የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጂቡቲ መሪዎች በተሳተፉበት የአራትዮሽ መድረክ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ በግብጽ እና ሳኡዲ አረቢያ ጉብኝት ያደረጉት የጦሩ አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጀነራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ በካርቱም ሰላም ለማስፈን ስለሚደረጉ ድርድሮች እና በሱዳን ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሱዳን ጦርነትን ሽሽት ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናውያን እና የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በመተማ፣ ጋምቤላ እና ኩምሩክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፤ ከ34 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንንም ከጦርነት ቀጠና ማስወጣት መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።