በሱዳን ሰላም ለማስፈን ያለመ ምክክር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል
ለአራት ቀናት በሚካሄደው ምክክር ላይ ከ80 በላይ የፖለቲካ፣ ሲቪል ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል የጀመሩት ጦርነት ስድስት ወራት አስቆጥሯል
በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የሲቪል የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ያለመ ምክክር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የሱዳን ሁሉንም የሲቪል ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት ተወካዮች ያካተተው ምክክር በትናንትናው እለት ነው የተጀመረው።
በካርቱም ፖለቲካ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችም ለአራት ቀናት በሚቆየው ምክክር ተጋብዘው በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በአዲስ አበባው ምክክር እየተሳተፉ ከሚገኙ የሱዳን ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል።
ምክክሩ በህዳር ወር አጋማሽ ለሚደረገው የሲቪል ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባኤ የጋራ የሆነ አጀንዳ የሚቀረጽበት ነው ተብሏል።
የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) ጦርነት ከተጀመረ ስድስተኛ ወሩን ይዟል።
ጦርነቱን ለማስቆም በአዲስ አበባ፣ ካይሮ እና ጂዳ የተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶችም እስካሁን ፍሬ አላፈሩም።
የሱዳን የሲቪል ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት በቀጣይ ጦርነቱን ለማስቆምና የሲቪል የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ግዙፍ ምክክር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።
እስከ ማክሰኞ በሚቀጥለው የአዲስ አበባው ምክክር ጦርነቱን የሚያስቆምና ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማስፈን የሚረዳ የፖለቲካ ሂደት ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር በሚያዚያ ወር 2019 በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ካርቱም ይበልጥ ውጥረት ነግሶባታል።
አል በሽርን ተባብረው ከስልጣን ያነሱት ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎም የሲቪል የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ከማድረግ ይልቅ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
በዚህም ከ9 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ተቀጥፎ ከ4 ሚሊየን በላይ ሰዎችን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለመፈናቀል ተገደዋል።