በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሃን ጦር በኩል እስካሁን ስለ ጥቃቱ የተባለ ነገር የለም
በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ህንጻ ላይ የአየር ድብደባ እንደተፈጸመበት ተገለፀ።
የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኃይል (አር.ኤስ.ኤፍ) ቃል አቀባይ በትዊተር ገጽ ባሰራጨው መግለጫ፤ በካርቱም ከተማ አል-አማራት አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ህንጻ ላይ በሌ/ጄነራል በአል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር የአየር ኃይል በቦምብ ደብድቧል ብሏል።
የአየር ድብደባው የኤምባሲው ህንጻ ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱንም የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኃይል በመግለጫው አስታውቋል።
በአየር ድብደባው በኤምባሲው ውስጥ ሰዎች ስለመኖራቸው እና በሰዎች ስለደረሰው ጉዳት ግን እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።
የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኃይል (አር.ኤስ.ኤፍ) በመግለጫው አክሎም ላይ በሌ/ጄነራል በአል ቡርሃን የሚመራው ጦር የዲፕሎማቲክ ማእከላት ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያወቀግዝ አስታውቋል።
በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ስለደረሰው ጥቃት በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሐን ኃይሎች በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በፈረንጆቹ ሚያዝያ 15 የተጀመረው የሱዳን ጦርነት እንዲቆም በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢፈረሙም ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ይህ ጦርነት በሪያድ፣ በአዲስ አበባ እና ካይሮ ውይይቶች ቢደረጉም ተፋላሚዎች ተኩስ ማቆም አልቻሉም።
አጋር በነበሩት ጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ደጋሎ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ስድስት ወራትን አስቆጥሯል።
በጦርነቱ እስካሁን አራት ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከሀገራቸው ተሰድደዋል።