ኢትዮጵያ በሱዳን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ዜጎቿን እያስወጣች መሆኑን ገለጸች
ኢትዮጵያዊያኑ በአራት አውቶቡስ እንዲወጡ ተደርጓል ተብሏል
በሱዳን የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ሰባተኛ ወሩ ላይ ይገኛል
ኢትዮጵያ በሱዳን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ዜጎቿን እያስወጣች መሆኑን ገለጸች።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል ጦርነት የተጀመረው።
ይህ ጦርነት ከሱዳናዊያን በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ዜጎችን ጎድቷል።
ለደህንነታቸው በመስጋትም 100 ሺህ ገደማ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመተማ፣ ጋምቤላ እና ኩምሩክ በኩል እንደገቡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም ከሰሞኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በሱዳን መዲና ካርቱም ጨምሮ ሌሎች የጦርነት ቀጠና በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን የማስወጣት ስራ መቀጠሉን ገልጿል።
ሚንስቴሩ በመግለጫው በሱዳን የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ በተለያዩ ምክንያቶች ለመውጣት ያልቻሉትን እና ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት መንግሥት በጀት መድቦ እየሰራ እንደሆነም አስታውቋል።
ዜጎችን ከሱዳን የማስወጣት ሥራው በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ግብረኃይል ተመላሾችን ያሳፈሩ አራት አውቶቡስ ከካርቱም በመተማ በኩል ገብተዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት ከ34 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ከጦርነት ቀጠና ማስወጣቱን ገልጿል።