የሱዳኑ መሪ አል-ቡርሃን የሰራተኛ ማህበራት እንቅስቃሴ እንዲቆም ትእዛዝ አስተላለፉ
አል-ቡርሃን ጥቅምት 2021 ከወሰኑት ውሳኔ በኋላ ሱዳን በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደተዘፈቀች ነው
የአል-ቡርሃን እርምጃ በማህበራቱ ውስጥ ያለው የቀድሞ ገዥ እስላሞችን ተጽእኖ ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን በሀገሪቱ የሚገኙትን የሰራተኛ ማህበራት፣ የሙያ ፌዴሬሽኖች እና የጠቅላላ አሰሪዎች ፌዴሬሽን እንቅስቃሴ እንዲቆም ውሳኔ አስተላልፈዋል።
አል በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ባሉት አመታት ውስጥ እንደ የጋዜጠኞች እና ጠበቆች የመሳሰሉ በርካታ ሙያዎች ማህበራቸውን እንደገና መቋቋማቸው የሚታወቅ ነው፡፡
እንደገና በተቋቋሙት ማህበራት ውስጥ የቀድሞ ገዥ እስላሞችን የበላይነታቸውን መያዛቸውም ይነገራል፡፡እናም የአሁኑ የአል-ቡርሃን ትእዛዝ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ተጽእኖ ለመግታት የሚደረግ ሙከራ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡
የሱዳን የዜና አገልግሎት ሱና እንደዘገበው ሌ/ጀኔራል አል-ቡርሃን የሚመለከታቸው አካላት ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሱዳን ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ያሉትን ማህበራት ፋይናንስ የሚገመግም እና የሚቆጣጠር ኮሚቴ እንዲቋቋም ቡርሃን ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
በ"ነጻነት እና ለውጥ" ጥምረት የሚመሩ የሲቪል ሃይሎችን ያካተተው የሉዓላዊነት ምክር ቤት ወታደራዊ አካል ከ"ነጻነት ሃይሎች" ጋር በቅርቡ የማዕቀፍ ስምምነት እንደማይፈራረም ከሶስት ቀናት በፊት አስታውቋል፡፡
በዚህም በሱዳን ቀውስ ውስጥ ያሉ ወገኖች የሚያወጧቸው እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ መግለጫዎች በሱዳን የተጀመረው የመፍትሄው እርምጃ ወደ ኋላ እንዳይመልሱት ተሰግቷል፡፡
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌ/ጄነራል አብዱልፈታህ አል- ቡርሃን ጥቅምት 25 ቀን 2021 ከወሰኑት ውሳኔ በኋላ ሱዳን በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደተዘፈቀች ነው፡፡
ቀውሱ ያሳሰባቸው ሌ/ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የሱዳናውያን ፍላጎት እውን እንዲሆን የተቻላቸውን ጥረት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አል-ቡርሃን እሳቸው የሚመሩት የሱዳን ጦር ከፖለቲካዊ እርምጃ ራሱን ለማግለልና ሲቪል መንግስት ሲቋቋም ስልጣኑን ለማስረከብ ቁርጣኛ መሆኑም ነበር የተናገሩት፡፡
የሱዳን ህዝብ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳተፉበት እና ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበት ብሄራዊ መግባባትን በጉጉት እንደሚጠብቁም አል-ቡርሃን ከአልማርክያ ወታደራዊ ሰፈር ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል።
የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል ፕሬዝዳንቱ።