የሱዳን ጦር እራሱን ከፖለቲካዊ እርምጃ ለማራቅ ቁርጠኛ ነው - ሌ/ጄነራል አል-ቡርሃን
አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳን አሳሳቢ የሚባል የፖለቲካ ቀውስ በማስተናገድ ላይ መሆኗ ይታወቃል
አል-ቡርሃን የሱዳን ህዝብ እውነተኛ ለውጥ የሚፈልጉትን እስኪያገኝ ድረስ ጦሩ ከጎኑ ይቀማል ብለዋል
የሱዳን የሉዓላዊነት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ጦር ከፖለቲካዊ እርምጃ ራሱን ለማግለል ቁርጣኛ መሆኑን ተናገሩ።
የሱዳን ህዝብ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳተፉበት እና ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበት ብሄራዊ መግባባትን በጉጉት እንደሚጠብቁም አል-ቡርሃን ከአልማርክያ ወታደራዊ ሰፈር ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል።
የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል ፕሬዝዳንቱ።
አል-ቡርሃን ንግግራቸው ሲቀጥሉ " የተቋቋመው ኮሚቴ የአክራሪነት፣ የሽብርተኝነት እና ሌሎች አሉታዊ ክስተቶችን ለመጋፈጥ ብቁ ነው ብለን እናምናለን" ብለዋል።
ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ባለፈው ሳምንት ጦሩ የሱዳን ህዝብ እውነተኛ ለውጥ የሚፈልጉትን እስኪያገኝ ድረስ ከጎኑ እንደሚሆን ቃል ገብቷል ማለታቸው አይዘነጋም።
የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲያበቃ በሲቪል አካላት (የነጻነት እና የለውጥ ሃይሎች) እና በወታደራዊ ሃይሎች መካከል በቅርቡ ከስምምነት ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የሱዳን መገናኛ ብዙሀን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሁለቱ የፖለቲካ መካረር ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ በመዘገብ ላይ ናቸው።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳን አሳሳቢ የሚባል የፖለቲካ ቀውስ በማስተናገድ ላይ መሆኗ ይታወቃል።