የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት ሊቀመንበር ከግብፅ የደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጋር ተገናኙ
ባለፈው ሳምንት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወኪልን ለማብራሪያ መጥራቱ ይታወሳል
ሁለቱ አካላት በጋራ ጥቅም የጋራ ተግባር ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል
የሱዳንሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናንት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው የግብፅ የደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል አባስ ካሚልን አስተናግደዋል፡፡ የሱዳን የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ሌተናንት ጄኔራል ጋማል አብደል መጅድም በውይይቱ ተሳትፈዋል።
በሁለቱ ወገኖች በጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ከሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ግንኙነታቸውን ለማዳበር እና የጋራ ትብብርን ለማጎልበት በሚያደርጉት የጋራ ተግባር ዙሪያም ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡
በውይይቱ ወቅት የሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ግብፅ በሁለቱ ሀገራት እና በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ባለው ታሪካዊና የሁለትዮሽ ግንኙነት ማዕቀፍ የሱዳንን ህዝብ በመደገፍ ለምታሳየው ወዳጅነትአድናቆታቸውን እንደቸሩም ተገልጿል፡፡ ለግብፅ ፕሬዝዳንት ያላቸውን አድናቆት እና ምስጋናም ገልጸዋል፡፡
የግብፅ ልዑካን ቡድን መሪ ሜ/ጄኔራል አባስ ካሚል ፣ ሱዳን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገሮች ዝርዝር በመውጣቷ ለሉዓላዊነት ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሱዳንን የሽግግር ምዕራፏን እንድታጠናቅቅ ግብፅ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡
የግብፅ ልዑካን አባላት ከሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሀምዳን ደጋሎ ጋርም ተመሳሳይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት እንዲፈጠር የሚሰሩ የውጭ ኃይሎች አሉ ማለታቸውን ተከትሎ ግብፅ ቅሬቷን ማሰማቷ ይታወሳል፡፡
በአምባሳደር ዲና ንግግር ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወኪልን ጠርቶ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ዲና “የሱዳንን ሰፊ መሬትን የያዙ አሉ፤ ግን ለሱዳን ተቆርቋሪ እየመሰሉ ይረብሻሉ” ያሉት ቃል አቀባዩ “ስማቸውን መናገር ግን አልፈልግም ፤ እናንተው ታውቋቸዋላችሁ” ሲሉ ማንነታቸውን በግልጽ ሳይጠቅሱ ማለፋቸው ይታወሳል፡፡
“አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግብጽን በተመለከተ ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት ሰጥተዋል” ያሉት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር አሕመድ ሀፊዝ “ግብፅ የግድቡን ግንባታ የምትቃወመው በሀገሪቱ ያለባትን ቀውስ ለማቀዝቀዝ ነው ማለታቸው ተገቢ አስተያየት አይደለም” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው “እኔ ቀጣናውን የሚረብሹ፤ ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿን ማበጣበጥ የሚፈልጉ አካላት አሉ አልኩ እንጂ እከሌ ነው የሚል የሀገር ስም አልጠራሁም” ሲሉ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
“ነገር ግን ሌባ እናት ልጇን ስለማታምን ይህንን የምናደርገው እኛ ነን ካሉ ምንም ማድረግ አንችልም” ሲሉም አምባሳደር ዲና በወቅቱ ተናግረዋል፡፡