ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ተቀባይነት ሲያገኝ ግብጽ ፈጽሞ አልቀበልም ብላለች
የግድቡ ሙሌት እና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት መደረሱ ተገልጿል
የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሶስትዮሽ ስብሰባውን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት በበይነ-መረብ ስብሰባ አካሂደዋል። ስብሰባው በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።
ሚኒስትሮቹ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በማተኮር ምክክር መደረጉን የዉሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ባለሙያዎቹ የቀረጹትን ሰነድ በበጎ እንደምትመለከተው እና በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ የሱዳን ወገን በበኩሉ ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጎ እንደሚመለከተው እና በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ሚና ላይ በጋራ በማጽደቅ ድርድሩን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ የግብጽ ወገን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው መግለጹንም ነው የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለከተው፡፡
የሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት ቢሆንም፣ ወደፊት በዓባይ ተፋሰስ ላይ ከሚገነቡ የውሃ ልማት ሥራዎች ጋር የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሃሳብ ነው ብሏል ሚኒስቴሩተ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍጆታ የሌለው የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደመሆኑ በግድቡ ላይ የሚደረሰው ስምምነት ይህንኑ ከግምት ያስገባ እና የተሟላ የውሃ ስምምነት በሌለበት እና ኢፍትሃዊ አጠቃቀም በሰፈነበት ተፋሰስ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን ኢትዮጵያ እንደማትፈቅድም ተገልጿል፡፡
ይህን መሰረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ አሞላል እና ዓመታዊ አስተደዳር የሚመለከተውን ደንብ በጋራ ስምምነት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ ናት ያለው መግለጫው በዚህም መሰረት የስምምነት አማራጮችን ለግብጽ እና ሱዳን ወገን ያቀረበች ሲሆን የሃገራቱ ምላሽ ቀና እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል ብሏል፡፡
በቀጣይ የሃገራቱ ባለሙያዎች በውሃ ሚኒስትሮች አመራር ስር ስብሰባቸውን በመቀጠል ስምምነት የተደረሰባቸውን እና የልዩነት ሃሳቦችን በመለየት በቀጣይ ዕሁድ ጥር 01 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው የስድስት ሚኒስትሮች ስብሰባ ውጤቱን ያቀርባሉም ተብሏል፡፡