“በምርጫ ካልሆነ በስተቀር ስልጣን አሳልፈን አንሰጥም”- የሱዳን ጦር መሪ
ከአሁን በኋላ የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን እንደማይታገሱም ነው የጦር መሪው የተናገሩት
አል ቡርሃን ሱዳናውያን ለሚመርጡት አካል ስልጣን እናስረክባለን ሲሉ ተናግረዋል
የሱዳን ጦር በምርጫ አለበለዚያም በፖለቲካዊ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ስልጣን አሳልፎ እንደማይሰጥ የጦሩ መሪ ተናገሩ፡፡
ጄ/ል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ሱዳናውያን ለሚመርጡት አካል ስልጣን እናስረክባለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት ትናንት ረቡዕ በሰሜናዊ ዳርፉር አል-ፋሸር ከተማ ለሰራዊቱ የእግረኛ ጦር አባላትና አመራሮች ባደረጉት ንግግር ነው።
በንግግሩ በየትኛውም የሃገሪቱ ጫፍ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለ ነው በሚል ያወደሱት ጦሩ ዜጎችን እና የሃገሪቱን ድንበር ነቅቶ እንዲጠብቅና ከአካባቢው ተፈናቅለው የነበሩ እንዲመለሱ አሳስበዋል፡፡
ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና የሃገሪቱን ክብር ለመጠበቅ አዲስ የጸጥታና ደህንነት መመሪያዎች ተላልፈው መተግበር መጀመራቸውንም ነው ቡርሃን ያስታወቁት፡፡
የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ጄ/ል ሞሃመድ ሃምዳን ዳገሎ በበኩላቸው የሃገሪቱ ሰላምና ደህንነት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተላልፈው ጥሰት የሚፈጽሙትን መታገስ እንደማይገባም ነው ዳገሎ የተናገሩት፡፡
ወታደራዊ ሃይሉ ስልጣን እንዲለቅ የሚያሳስቡ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ፖለቲከኞች ዘንድ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችል ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የድርጅቱን ተወካዮች አካሄድ የተቹ የሱዳን ባለስልጣናት ተመድ በሱዳን ቀውስ ጉዳይ “አስተባባሪ እንጂ አስታራቂ መሆን የለበትም"ሲሉ ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡