የሱዳን ሉአላዊ ም/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ ገቡ
ሌ/ ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ
የሉአላዊ ም/ቤቱ ም/ፕሬዝዳንት በቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸውን የሱና ዘገባ ያመለክታል።
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ እና ልኡካቸው በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ ከተለያዩ የመንግሰት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
በዉይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የሁለቱን ሀገራ ፍላጎት ማስጠበቀ መልኩ የጋራ ጉዳዮችን ማሳደግ እና መደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉም ተብሏል።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከተጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ወደ ከረረ አለመግባባት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ትግራይ ክልል ባዘመተበት ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት እንደመልካም አጋጣሚ በማየት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቷል በማለት ኢትዮጵያ ትከሳለች። ሱዳን ክሱን ትቀበለውም።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር በተለያየ ጊዜ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ድንበር እስካሁን መሬት ላይ ያልተሰመረ መሆኑ ሌላኛው ያለመግባባት ምክንያት ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው፤ ይህን ገዳይ ለመፍታት ሀገራቱ የጋራ የድንበር ኮሜቴ በፈረንጆቹ 2020 አቋቁመዋል።