ኢጋድ በራሳቸው በሱዳናውያኑ ባለቤትነት የሚመራውን የለውጥና ሽግግር ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመምከር ካርቱም ናቸው፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ በሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስና መፍትሄዎቹ ዙሪያ ለመምከር ትናንት እሁድ ነው ካርቱም የገቡት፡፡
ከኢጋድ የሱዳን አምባሳደር ጋርም በሃገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታም ላይ መክረዋል፡፡
በምክክሩ በሱዳን በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎችም ነበሩ፡፡
ቀጣናዊው ተቋም ኢጋድ በሱዳናውያን ባለቤትነት የሚመራውን የለውጥና ሽግግር ሂደት መደገፍ አለበት በሚል ተሳታፊዎቹ ማረጋገጣቸውንም ዶ/ር ወርቅነህ በይፋዊ ማህበራዊ ገጾቻቸው አስታውቀዋል፡፡
ተቋማቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ነው ዋና ጸሃፊው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን የተደረገውን የፖለቲካ ስምምነት አደነቀ
ዛሬ ጠዋትም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ እና የተመድ የሱዳን ተልዕኮ ዋና ኃላፊ ከሆኑት ቮከር ፐርዝ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡
ፐርዝ ሱዳናውያኑ በችግሮቻቸው ዙሪያ እንዲነጋገሩ ለማድረግ በተመድ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በማስፈጸም ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም ቮከር ፐርዝስ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገቡ ነው በሚል የወቀሱት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ/ል ሃምዳን ዳገሎ ሰውዬው አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደሉም ሲሉ ድርጊቱን ማውገዛቸው ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ የሱዳን ተልዕኳቸውን በተመለከተ ከአውሮፓ ህብረት እና ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኖርዌይ (ትሮይካ) ተወካዮች ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውንም ተቋማቸው አስታውቋል፡፡
ሱዳን የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ናት፡፡ የቀድሞው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት ተቋሙን በሊቀመንበርነት ይመሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡