ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት የአል ፋሽቃ የድንበር አካባቢ የገነባቻቸውን መሰረተ ልማቶች አስመረቀች
ቡርሃን “አል ፋሽቃን ማስመለስ የሱዳን ህዝብን እና የጦሩን ክብርን ማስመለስ ነው” ሲሉ በስነ ስርዓቱ ተናግረዋል
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ተገኝተዋል
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት የአል ፋሽቃ የድንበር አካባቢ የገነባቻቸውን መሰረተ ልማቶች አስመረቀች፡፡
ድልድይን ያካተቱት መሰረተ ልማቶቹ በአካባቢው ማህበረሰብ ትንሹ እና ትልቁ በሚል የሚታወቁ የአል ፋሽቃ አካባቢዎችን የሚያገናኙ ሲሆን በትልቁ አል ፋሽቃ ነው የተገነቡት፡፡
ከአብደራፊ እና አሲራ ጋር የሚዋሰነው ትልቁ አል ፋሽቃ እስከ መተማ የሚደርስ አዋሳኝ የድንበር አካባቢ፡፡ በልጉዲ በኩል ማይካድራን የሚያዋስነው ደግሞ ትንሹ አል ፋሽቃ በሚል ይታወቃል፡፡
መሰረተ ልማቶቹ የሱዳን ጦር የተመሰረተበትን 67ኛ ዓመት ክብረ በዓል ታሳቢ አድርገው ‘ዋድኮሊ’ በተባለ አካባቢ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት የተመረቁ ናቸው፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና ሌሎች ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ንግግር ያደረጉት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን “አል ፋሽቃን ማስመለስ የሱዳን ህዝብን እና የጦሩን ክብርን ማስመለስ ነው” ብለዋል፡፡
በዓሉ በዋድኮሊ መከበሩ “የአል ፋሽቃን የሱዳን መሬትነት የሚያረጋግጥ እና ጦሩ መሬቱን ለማስመለስ የከፈለውን መስዋዕትነት” የሚያሳይ እንደሆነም ነው ቡርሃን የተናገሩት፡፡
አካባቢው የሱዳን መሆኑን የማረጋገጡ ጉዳይ በአል በሽር የስልጣን ዘመን በነበሩ ፖለቲከኞች “ድክመት” መጓተቱን ቡርሃን አንስተዋል፡፡ እ.ኤ.አ 2017 ላይ ጀበል ሎባን አካባቢ የነበረው የሃገሪቱ ጦር አካባቢውን ከኢትዮጵያ ለማስለቀቅ ተዘጋቶ እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም ጦሩ ኦፕሬሽኑን አቁሞ ለቆ እንዲወጣ ፖለቲከኞቹ በመወሰናቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አሁን ግን ጦሩ መልሶ ይዟቸዋል ባሏቸው መሬቶች ላይ የመሰረተ ልማት ግንባታው እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ቡርሃን በመሬቶቹ ዙሪያ ለመደራደር የተደረጉ ጥረቶች “ኢትዮጵያ ጉዳዩን በመጓተቷ ምክንያት ሳይሳኩ ቀርተዋል” ያሉም ሲሆን ቀሪ መሬቶችን “በድርድር አለበለዚያም በሌሎች አማራጮች” እንደሚያስመልሱ ተናግረዋል፡፡ “ሌሎች” ያሏቸው አማራጮች ምን እንደሆኑ ግን በውል አላስቀመጡም፡፡
የሱዳን ጦር ካሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ወዲህ የያዛቸው እነዚህ የአል ፋሽቃ አካባቢዎች ኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬቶቼ ናቸው የምትላቸው ናቸው፡፡ በወረራው እስከተያዙበት ጊዜ ድረስም ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ስር ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር ከያዛቸው ሉዓላዊ የኢትዮጵያ መሬቶች ለቆ እንዲወጣ እና ከአሁን ቀደም የተጀመሩ ድርድሮች እንዲቀጥሉ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ድልድይና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መገንባቱን እንዲያቆም ጭምር አሳስባ እንደነበር መገለጹም የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም ሱዳን ከድርጊቷ አልታቀበችም፡፡ ይልቁንም የጦር ሰፈሮችን በአካባቢው ስለ መገንባት ማሰቧ ነው የሚነገረው፡፡