ወደ ካርቱም ተጠርተው የነበሩት በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ
ሱዳን አሁንም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓትን ማደራደር እፈልጋለሁ ብላለች
ሱዳን ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሯን ወደ ካርቱም እንዲመለሱ ጠርታ ነበር
ወደ ካርቱም ተጠርተው የነበሩት በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት አገራቸው አሁንም ኢትዮጵያን መርዳት ትፈልጋለች፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ችግር ላይ በነበርንበት የሽግግር ጊዜ እኛን መጥቶ ለመርዳት ፈቃዳችን አላስፈለገውም ነበር፤ እና እኛም ብድር የመመለሻችን ጊዜ አሁን ነው ብለን እናስባለን፤ ምክንያቱም አንድነቷ እና ደህንነቷ የተጠበቀ፣የተረጋጋች ኢትዮጵያን ማየት ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በምንመራው ቀጣናዊ ተቋም ኢጋድ በኩል ይህን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብንም እናስባለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫው መናገራቸውን አል ዐይን አማርኛ ከጽህፈት ቤታቸው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሱዳን የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀመንበር ናት፡፡ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያን መንግስት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር ለማደራደር ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከሩዋንዳው ፖል ካጋሜ፣ ከደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎዛ እና ከአሜሪካ ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ካርቱም ተጠርተው የነበሩት በአዲስ አበባ የሱዳን አምባሳደር ከዛሬ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውንም ሃምዶክ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በወቅቱ ወደ ካርቱም የተጠሩት ሱዳን የፌደራል መንግስቱን እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር ላደራድር በሚል ላቀረበችው ጥያቄ ኢትዮጵያ ፈቃደኛ አለመሆኗን ተከትሎ ከመንግስታቸው ጋር ለመመካከር ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በሀይል በመያዟ ለማደራደር ተዓማኒነት ይጎድላታል” ማለታቸው ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ሱዳን በአዲስ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደሯን ወደ ካርቱም እንዲመጡ መጥራቷን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳወቁ ይታወሳል።