ሱዳን ከማክሰኞ ጀምሮ ግጭት አንደነበር ብትገልጽም የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊት ስለጉዳዩ መረጃ አልደረሰኝም ብሏል
ሱዳን ከማክሰኞ ጀምሮ ግጭት አንደነበር ብትገልጽም የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊት ስለጉዳዩ መረጃ አልደረሰኝም ብሏል
ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ አለመግባባት መቀስቀሱን የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የደረሰው መረጃ እንደሌለ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡ የሰራዊቱ የኢንዶክትሪኔሽንና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ እንዳሉት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም መረጃ እንደሌላቸውና ከሌሎች የሰራዊቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ አሚን መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) እንዳሉት ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” አትባራ ወንዝ ውሃ ሊቀዱ መሄዳቸውንና ከሱዳን ወታደሮች ጋር አለመግባባት መፈጠሩን ገጸዋል፡፡
የሱዳን ወታደሮች “የኢትዮጵያን ታጣቂዎች” ውኃ አትወስዱም በማለታቸው አለመግባባቱ ወደ ግጭት ማምራቱን አስታውቀዋል፡፡ ግጭቱ ሲፈጠር “ከኢትዮጵያ ታጣቂዎች አንዱ ተመታ፤ የኢትዮጵያ ታጣቂዎች ተመልሰው ሄዱ” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ “የኢትዮጵያን ታጣቂዎች” ውኃ ወደሚቀዳበት ቦታ ተመልሰው መምጣታቸውንና ሲመጡም በመከላከያ ሰራዊት ታግዘው እንደነበር የገለጹት ቃል አቀባዩ አሚን መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) የመጡበት ቦታ የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ስለነበረ ግጭት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ሁለቱ ኃይሎች ድርድር መጀመራቸውንና “ከኢትዮጵያ ታጣቂዎች” በኩል “ውኃ መውሰድ አለብን ፣እርሻም ማረስ አለብን” የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን አንስተዋል፡፡
በስፍራው ያለው የሱዳን መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ ”ውሃ አትወስዱም፣ እርሻም አታርሱም፣ በፍጹም አይሆንም” እንዳላቸው እና “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” ”አስፈራርተው” መመለሳቸውን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ሂደት በኋላ “የኢትዮጵያን ታጣቂዎች” ወደ ሥፍራው በድጋሚ መምጣታቸውን የገለጹት ዶ/ር አሜር መሐመድ ሐሰን ተኩስ እንደተከፈተና በዚህም “አንድ የሱዳን ኮማንደር መገደሉንና ስድስት ወታደሮች መቁሰላቸውን” ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
“ውጊያው በከባድ መሳሪያ የታገዘ” እንደነበር ያነሱት ቃል አቀባዩ ከአንድ ኮማንደር መገደልና ከስድስት ወታደሮች መቁሰል በተጨማሪ አንድ ህጻን ሞሙቱንና ሌላ ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ግጭቱ ወደተቀሰቀሰበት ቦታ ተጨማሪ ኃይል መላኩንና ታጣቂ ያሏቸው ከሱዳን ግዛት እንዲወጡ መደረጉን የሱዳን ዜና አገልግሎት በትናንትናው እለት ዘግቦ ነበር፡፡
በከ10 ቀናት በፊት የኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ በአዲስ አባባ ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይና አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታና ደህንነት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታውሳል፡፡ በውይይቱ በአዋሳኝ አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ተስማምተው ነበር፡፡
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ድንበር ባለመካለሉ ምክንያት በተለያየ ጊዜ ግጭት ሲቀሰቀስ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡