ኔይማር ከሮናልዶ እና ቤንዜማ በመቀጠል ለሳኡዲ ክለብ የፈረመ ዝነኛ አጥቂ ሆኗል
ብራዚላዊው አጥቂ ኔይማር ጁኒየር ለሳኡዲው ክለብ አል ሂላል ፊርማውን አኖረ።
የ31 አመቱ ተጫዋች የዝውውር ዋጋ በይፋ ባይገለጽም እስከ 90 ሚሊየን ዩሮ ይደርሳል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ኔይማር በአል ሂላል ለሁለት አመት የሚያቆየውን ውል የተፈራረመ ሲሆን በአመት 150 ሚሊየን ዩሮ እንደሚከፈለው ቢቢሲ ዘግቧል።
በፒኤስጂ በአመት 25 ሚሊየን ዩሮ ያገኝ የነበረው ተጫዋቹ በሳኡዲው ክለብ ከስድስት እጥፍ በላይ ያገኛል ነው የተባለው። የተጫዋቹ አመታዊ ክፍያ 100 ሚሊየን ዩሮ ነው የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ይገኛሉ።
የ31 አመቱ ኔይማር “በሳኡዲ ፕሮ ሊግ አዲስ ታሪክ ማጻፍ እፈልጋለሁ” ብሏል።
የአል ሂላል ክለብ ሊቀመንበር ፋሃድ ቢን ሳድ በበኩላቸው፥ ኔይማር “አለማቀፍ የእግር ኳስ ምልክትና ፈጣን አጥቂ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የፈረንሳዩን ክለብ ፓሪስ ሴንት ጀርሜን በ2017 ክብረ ወሰን በሆነ 200 ሚሊየን ዶላር የተቀላቀለው ኔይማር ለክለቡ 173 ጊዜ ተሰልፎ 118 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በስድስት አመት ቆይታው አምስት 13 ዋንጫዎችን ማንሳትና በ2020ም የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መድረስ ችሏል።
በዚህ አመት የቀድሞዎቹን የባርሴሎና ከዋክብት ሊዮኔል ሜሲ እና ኔይማርን ያጣው ፒኤስጂ ኪሊያን ምባፔም ከአል ሂላል ጋር እንዲደራደር መፍቀዱ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ወደ ባርሴሎና ሊመለስ እንደሚችል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ኔይማር አል ሂላልን ተቀላቅሏል፤ ምባፔም በፒኤስጂ ለአንድ አመት ቆይታውን የሚያረዝም ውል መፈረሙ ተነግሯል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ አል ናስር መዘዋወሩን ተከትሎ ለሳኡዲ ክለቦች የሚፈርሙ ታዋቂ ተጫዋቾች ቁጥር ጨምሯል።
ካሪም ቤንዜማ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ ጆርዳን ሄንደርሰን እና ሮቤርቶ ፊርሚኖን ጨምሮ በአውሮፓ ሊጎች ዝናን ያተረፉ ተጫዋቾች የሳኡዲ ፕሮ ሊጅ መጀመርን እየተጠባበቁ ነው።