ኔይማር በሀገሩ የ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ተላለፈበት
ብራዚላዊው አጥቂ በቅንጡ መኖሪያ ግቢው ያለፈቃድ ሰው ሰራሽ ሃይቅ በመገንባቱ ነው ቅጣት የተጣለበት
ኔይማር በ20 ቀናት ውስጥ ይግባኝ መጠየቅ ይችላል ተብሏል
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ኔይማር በሀገሪቱ ፍርድ ቤት የ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል።
ኔይማር ከሪዮ ዴኔኔሮ በ130 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማንጋራቲባ ባለው ቅንጡ መኖሪያ ቤቱ በገነባው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ምክንያት ነው ቅጣቱ የተጣለበት።
የ31 አመቱ ተጫዋች ሰው ሰራሽ ሃይቁን ሲገነባ ከአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ፈቃድ ባለመውሰድ አራት ክሶች ቀርበውበታል።
የፒኤስጂው አጥቂ ባለፈው ሰኔ ወር በመኖሪያ ቤቱ ባዘጋጀው ድግስ በስው ሰራሽ ሃይቁ ሲዋኝ መታየቱን ተከትሎ ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል።
የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣናትም ኔይማር ምንም አይነት ፈቃድ ሳይጠይቅ ሰው ሰራሽ ሃይቁን መገንባቱን በመቃወም ግንባታው እንዲቆም ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታውሷል።
ያለህጋዊ ፈቃድ የወንዝ ውሃን አቅጣጫ አስቀይሮ ወደ ሰው ሰራሽ ሃይቁ ማስገባትን ጨምሮ የደን ምንጣሮ እና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ህግን የሚጻረሩ ተግባራትን ፈጽሟል የሚል ክስም ቀርቦበታል።
በትናንትናው እለትም ተጫዋቹ የ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ተላልፎበታል።
የኔይማር የህዝብ ግንኙነት ስለጉዳዩ እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም።
ህጋዊ ፈቃድ በሌለው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ግንባታ ምክንያት ቅጣቱ የተጣለበት ብራዚላዊው ተጫዋች በ20 ቀናት ውስጥ ይግባኝ መጠየቅ ይችላል ተብሏል።
ኔይማር በ2016 የገዛው ቅንጡ ግቢ 10 ሺህ ስኩዌር ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፥ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ ጂም እና ቅጣት ያስከተለበት ሰው ሰራሽ ሃይቅን ይዟል።
በኳታሩ የአለም ዋንጫ በቁርጭምጭሚቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የቀዶ ህክምና ያደረገው ኔይማር ከየካቲት ወር 2023 ወዲህ ጨዋታ አላደረገም፤ በፒኤስጂ የመቆየቱ ነገርም አጠራጣሪ ነው ተብሏል።