ፒኤስጂ ብራዚላዊውን አጥቂ ኔይማርን ለአል ሂላል ለመሸጥ ተስማማ
ዝውውሩ እንዲጠናቀቅ የ31 አመቱ ኔይማር የጤና ምርመራ እና ሌሎች ማሟላት ያለበትን ቅደመ ሁኔታዎች ማጠናቀቅ ይኖርበታል
ፒኤስጂ ብራዚላዊውን አጥቂ ኔይማርን ለሳኡዲ ፕሮሊጉ አል ሂላል በ90 ሚሊዮን ዩሮ ለመሸጥ መስማማቱ ተገልጿል
የፈረንሳዩ ክለብ ፖሪስ ሴንት ጀርሜን (ፒኤስጂ) ብራዚላዊውን አጥቂ ኔይማርን ለሳኡዲ ፕሮሊጉ አል ሂላል በ90 ሚሊዮን ዩሮ ለመሸጥ መስማማቱ ቢቢሲ ዘግቧል።
ዝውውሩ እንዲጠናቀቅ የ31 አመቱ ኔይማር የጤና ምርመራ እና ሌሎች ማሟላት ያለበትን ቅደመ ሁኔታዎች ማጠናቀቅ ይኖርበታል።
በፈረንጆቹ 2017 የዓለም ክብረወሰን በሰበረ 222 ሚሊዮን ዩሮ ፒኤስጂን የተቀላቀለው ኔይማር ቅዳሜ የተካሄደው በሊግ አንድ መክፈቻ ላይ አልተሳተፈም።
ኔይማር በአዲሱ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ሊዊስ ኢንርኬ አልተካተተም። ፒኤስጂ ትላልቅ ስም ያላቸውን ተጨዋቾች ከማስፈረም ወጥቶ አዲስ ስትራቴጂ እየተከቸለም መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ይጠቅሳል።
ኔይማር በፈንሳይ ቆይታው በአመት 25 ሚሊዮን ዩሮ ይከፈለው እንደነበር መረዳት ተችሏል። ኔማር ለፒኤስጂ 173 ጊዜ የተጫወተ ሲሆን ክለቡ አምስት የሊግ አንድ ጨምሮ 13 ዋንጫዎችን እንዲያገኝ እና በፈረንጆቹ 2020 የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ እንዲሆን አስችሎታል።
ነገርግን የኔይማር የፖሪስ ቆይታው በተደጋጋሚ በደረሰበት የቁርጭምጭሚት ጉዳት የተስተጓጎለበት ወቅት ነበር። የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች የሆነው ኔይማር ባለፈው መጋቢት ቀዶ ጥገዶ በማድረጉ በቀሪ የውድድር ዘመኑ ጨዋታዎች ላይ ሳይሳተፍ ቀርቷል።
ኔይማር በኳታሩ የአለም ዋንጫ ጨዋታም ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።
ከአለም ዋንጫ ጨዋታ በተጨማሪ በጉዳት ምክንያት በፈረንጆቹ 2019 በተካሄደው የኮፖ አሜሪካ ጨዋታ ላይም አልተሳተፈም።