የሱዳን ጦር ሌላኛው ተገዳዳሪ አብዱልአዚዝ አል ሂሉ ማን ናቸው?
በደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጥቃት መፈጸም መጀመሩ ተገልጿል
መገንጠልን የሚያቀነቅነው ሃይል የሱዳን ጦር ተፋላሚ ሆኖ ብቅ እያለ ነው ተብሏል
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ለ72 ስአት የደረሱት ተኩስ የማቆም ስምምነት ሳይጠናቀቅ በካርቱም፣ ኦምዱርማን እና ደቡብ ኮርዶፋን ውጊያው ተጀምሯል።
በጦርነቱ እንደ አዲስ ሆኖ የተከሰተው ነገር ግን የሱዳን ጦር በደቡብ ኮርዶፋን ከፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ውጭ በሆነ ቡድን ኢላማ የመደረጉ ጉዳይ ነው።
የሱዳን ጦር “ከሃዲ” ሲል በገለጸውና በአብዱል አዚዝ አል ሂሉ በሚመራው የሱዳን ነጻ አውጪ ግንባር ጥቃት ደርሶበት ወታደሮቹ መሞታቸውንና መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ሙሀመድ ዩሱፍ አል ሙስጠፋ የተባሉት የቡድኑ አመራር ግን አል ሂሉ የሚመሩት ሃይል ጥቃቱን አልፈጸመም ሲሉ የሱዳን ጦር መግለጫን ውድቅ ማድረጋቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር
የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ኤስፒኤልኤም) በደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል አካባቢ ለአመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየና በርካታ አካባቢዎችን የተቆታጠረ ቡድን ነው።
ደቡብ ሱዳን በፈረንጆቹ 2011 ከሱዳን ከመገንጠሏ በፊትም የአዲሲቷን ሀገር ምስረታ እውን ለማድረግ የሚዋጉ ሃይሎችን ሲያግዝ ቆይቷል።
የ22 አመቱን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ከተፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ጁባ አዲስ ሀገር ሆና ስትመሰረት ኤስፒኤልኤም ወደ በደቡብ ኮርዶፋን ወደ ትጥቅ ትግሉ ተመልሷል።
ግንባሩ በ2017ም ወደ ሁለት ተሰንጥቋል፤ በአብዱልአዚዝ አል ሂሉ (ኤስፒኤልኤም - ኤን) እና ማሊክ አጋር በሚመሩ ክንፎች።
ሁለቱ የኤስፒኤልኤም ክንፎች በጁባ ከሱዳን መንግስት ጋር ለድርድር ሲቀመጡም አል ሂሉ ረግጠው ወጥተዋል።
ማሊክ አጋር ግን ስምምነት ፈጽመው በሉአላዊ ምክርቤቱ የአልቡርሃን ምክትል ሆነዋል።
በ2020 ሱዳን በዳርፉር ከሚንቀሳቀሱና ከሌሎች ተፋላሚ ሃይሎች ጋር ስምምነት ስትፈጽምም የአል ሂሉ ክንፍ የሱዳን መንግስት ቅድመ ሁኔታዎቼ አልተከበሩም በሚል የስምምነቱ አካል አልሆነም።
ለደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲሰጣቸውም በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ተደምጧል።
ከሁለት አመት በፊት ግን የሱዳን መንግስት እና “ኤስፒኤልኤም - ኤን” በጁባ የመርህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
በዚህ ስምምነትም የታጠቁ ሃይሎችን የማዋሃድ እና ሴኩላር መንግስት የመመስረት ጉዳይ ቀዳሚው ነበር።
በሱዳን ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በወታደራዊ ትግል ሳይሆን በፖለቲካዊ ንግግር ነው ብለው በ19 መሰረታዊ ጉዳዮች የመርህ ስምምነት ሲፈራረሙ አራት ነጥቦች በይደር ቆይተዋል።
በሉአላዊ ምክርቤቱ ስልጣን የተነፈገው የሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሰሜን ክንፍ (ኤስፒኤልኤም -ኤን) አሁን ላይ የልዩነት ሰበዙን እየመዘዘ መጠቀም ሳይጀምር አልቀረም ተብሏል።
በደቡብ ኮርዶፋን በትናንትናው እለት ለደረሰው ጥቃትም የሱዳን ጦር ጣት የቀሰረው በዚሁ ተፋላሚ ሃይል ላይ ነው።
በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከሁለት ወራት በላይ መታመሷን የቀጠለችው ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎቿ ከሁለት ወደ ሶስት ከፍ ብለዋል።