የአረብ ኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ደማቅ የአዲስ አመት አቀባበል ክብረወሰን ሰብሯል
በ673 ድሮኖች የቀረበው ደማቅ የርችት ትዕይንት ለ12 ደቂቃዎች ቆይታን ያደረገ ነው
የአል ካይማህን ሰማይ ያደመቀው ትዕይንት እስከ ከ4 ነጥብ 7 ኪሎሜትሮች ድረስ በመታየቱም አዲስ ክብረወሰን ይዟል
የአረብ ኢምሬትሷ ራስ አል ካይማህ ከተማ የአዲስ አመት መግባት በጉጉት ከሚጠበቅባቸው ከተሞች አንዷ ናት።
ከተማዋ በደማቅ መብራቶች አሸብርቃ ሰማይ ላይ አስደናቂ ቅርጽ እና ህብር ያላቸው ርችቶችን እየተኮሰች አዲሱን አመት ትቀበላለች።
የዘንድሮውን አዲስ አመት 2023 ስትቀበልም ይሄው ድምቀቷ ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል ነው የተባለው።
በርችት ወይም ፋየርወርክ ትዕይንት በርካታ የአለም ክብረወሰኖችን የያዘችው ራስ አል ካይማህ፥ ሁለት ክብረወሰን ያሻሻለ ትዕይንት ለእይታ አቅርባለች።
671 ድሮኖችን ተጠቅማ የከወነችው ስነስርአት በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ እና የተለያየ ቀለማት ባላቸው መብራቶች ህብራዊ እንቅስቃሴ የታጀበ ነበር።
የ12 ደቂቃዎች ርዝማኔ ያለውን ትዕይንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሌሊት ተነስተው ተመልክተውታል፤ ከተለያዩ ሀገራት ይህንኑ ትዕይንት ለመመልከት የመጡ ጎብኝዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ።
“መልካም አዲስ አመት 2023” የሚሉና ሌሎች በአረብኛ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የአንድነት እሴት የሚያሳዩ መልዕክቶችም ቀርበዋል።
ርችቶቹ እስከ 1 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ድረስ የሚተኮሱ ስለነበሩም አል ማርጃን ከተባለችው ደሴት እስከ አል ሃምራ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተውታል።
ከ4 ነጥብ 7 ኪሎሜትር በላይ ርቀት ድረስ ታይቷል የተባለውን የአዲስ አመት መቀበያ በአካል መመልከት ያልቻሉትም በድረገጽ በቀጥታ መመልከታቸውን ዋም የዜና ወኪል ዘግቧል።
አይረሴ የአዲስ አመት ዋዜማ ለማሳለፍ ከ30 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን የራስ አል ካይማህ የቱሪዝም ልማት አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚው ራኪ ፊሊፕስ ይናገራሉ።
አል ካይማህን የ2023 የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም የዋዜማው ደማቅ ስነስርአት መነሻ እንደሚሆን ነው ያነሱት።
ከዱባይ፣ አቡዳቢ፣ ሻርጃህ፣ አል አይን እና አጅማን በመቀጠል 6ኛዋ ግዙፍ የኤምሬትስ ከተማ ራስ አል ካይማህ በቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት መነቃቃት እያሳዩ ከሚገኙት መካከል ትጠቀሳለች።