የሳኡዲ ብሄራዊ ቡድንም ሞሪንሆን በአሰልጣኝነት ለመቅጠር ፍላጎት ማሳየቱን ገልጿል
የሳኡዲው ክለብ አል ናስር ፖርቹጋላውያኑን ማጣመር እንደሚፈልግ ተገለጸ።
ክለቡ በሪያል ማድሪድ ከ2010 እስከ 2013 በአሰልጣኝነት እና ተጫዋችነት አብረው የሰሩትን ጆዜ ሞሪንሆ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዳግም ማገናኘት እንደሚፈልግ የስፔኑ አስ ጋዜጣ አስነብቧል።
አል ናስር ለጆዜ ሞሪንሆ አጓጊ ኮንትራት ማቅረቡንም ጋዜጣው አክሏል።
ክለቡ ማረጋገጫ ባይሰጥም የ60 አመቱ አሰልጣኝ በአመት 100 ሚሊየን ዩሮ እንዲከፈላቸው ጥያቄ ቀርቧል ብሏል አስ።
የጣሊያኑን ሮማ እያሰለጠኑ የሚገኙት ፖርቹጋላዊ በክለቡ እስከ 2024 የሚያቆይ ስምምነት አላቸው።
ሮማን የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮን የማድረግና በሴሪአው እስከ 4ኛ እንዲያጠናቅቅ የማገዝ ከፍተኛ ሃላፊነት ያላባቸው ሞሪንሆ፥ ከአል ናስር ቀርቦላቸዋል ለተባለው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
ፖርቹጋላዊው አወዛጋቢ አሰልጣኝ የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድንን እንዲያሰለጥኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል የሚሉ ዘገባዎች በቅርቡ ወጥተዋል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሩዲ ጋርሺያ ጋር የገባበት ፍጥጫ አልናስር አዲስ አሰልጣኝ እንዲያማትር ማድረጉ እየተነገረ ነው።
ከወደ ሪያድ የሚወጡ መረጃዎችም ሩዲ ጋርሺያ ከክለቡ ሳይለያዩ እንዳልቀሩና ለስንብቱም ሮናልዶን ተጠያቂ እያደረጉ ይገኛሉ።