የከርስቲያኖ ሮናልዶ “ፀጉር መሸበት” አድናቂዎቹን አስደንግጧል ተባለ
የሮናልዶ አድናቂዎች በእድሜውና በጸጉሩ በጨነቁም ተጨዋቹ ብቃቱን ማሳየት ቀጥሎበቃል
የ38 ዓመቱ ሮናልዶ በዩሮ-2024 የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት በምምራት የሚጫወት ይሆናል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንደፈረንጆቹ በ2003 አንጋፋውን የእንግሊዝ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋለ በዓለም እግር ኳስ መድረክ ነግሶ ለበርካታ ዓመታት መዝለቅ የቻለ ድንቅ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል።
ሮናልዶ በተጫወተባቸው አራት የተለያዩ ሊጎች ውስጥ የአውሮፓ ኃያላን ክለቦች የሚፋለሙበትን የቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ በርካታ ስኬቶችን መጎናጸፍ የቻለም ነው።
ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ የአምስት ጊዜ ባሎንደር አሸናፊው ሮናልዶ ድንቅ ብቃቱ ያስመሰከረባቸው ክለቦች መሆናቸውም አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ሮናልዶ ባሳለፍነው ዓመት በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ከአሰልጣኝ ቴን ሃግ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ኦልድ-ትራፎርድን ለቆ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አል-ናስር ሲቀላቀል በርካታ አድናቂዎቹ፤ የሮናልዶ እግሮች እንደወትሮ በእግር ኳስ ሜዳ ላናያቸው እየተቃረብን ነው በሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ይስተዋላል።
አድናቂዎቹ በምክንያትነት የሚያስቀምጡት ደግሞ ሮናልዶ አሁን ላይ በአውሮፓ ትላልቅ ሊጎች እየተጫወተ አለመሆኑ ነው።የሮናልዶን ጉዳይ የሚያሳስባቸው አድናቂቹ ጭንቀት ግን ይህ ብቻ አይደለም።
የ38 አመቱ የእግር ኳስ ኮከብ ሮናልዶ በሳኡዲ ፕሮ ሊግ ጎሎችን ማስቆጠሩ ቢቀጥልም ከሰሞኑ ልምምድ ላይ ሳለ “ጸጉሩ ሸብቶ” የሚሳይ ምስል መለቀቁ አድናቂዎቹን እጅግ ያስጨነቀ ጉዳይ ሆኗል።
በርካቶችም ከእድሜውና የጸጉሩ ሽበት ጋር በተያዘ ሮናልዶ ጫማውን ይሰቅላል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በሮናልዶ መሸበት ቁጭቱን የገለጸው አንድ ደጋፊ “አይሆንም ይህ ለእኔ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ ጫማ የሚሰቅልበትን ቀን ማየት የምችል አይመስለኝም፤ ጊዜው በጣም ይፈጥናል፤ የእግር ኳስ ህይወቱ ሲያጠናቅቅ መልካም ነገር ሁሉ ይገባዋል” ሲል ተናግሯል።
ሮናልዶ ፤ ጫማ ሊሰቅል ይችላል በሚል ለተጨነቁት እድናቂዎቹ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ፖርቹጋላዊው ኮከብ በቅርቡ በዩሮ 2024 ሀገሩን ወክሎ መጫወት እንደሚፈልግ መናገሩ አይዘነጋም።
የተመኘው አልቀረም የፖርቹጋሉ ዋና አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ሮናልዶ የብሄራዊ ቡድኑ አባልና አምበል አድርገው የመረጡት ከቀናት በፊት እንደነበርም የሚታወስ ነው።
አሰልጣኙ ስለ ሮናልዶ ሲናገሩ "ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለብሄራዊ ቡድኑ ከልቡ ሚጫወት የሆነ ተጫዋች ነው" ሲሉ ገልጸዋታል።
"እኔ እድሜን ወይም ሌሎች ገጽታዎችን አልመለከትም፤ ሮናልዶ አሁንም ቢሆን ቡድኑን የመርዳት እና ልምዱን ለሌሎች ተጫዋቾች የማስተላለፍ እድል አለው” ሲሉም ነው ማረቲኔዝ ከሮናልዶ እድሜ ጋር በተያያዘ ለተነሳለቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት።