አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሽያ፤ “ሮናልዶ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ነው” ብለዋል
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳኡዲ አረቢያ ያለው ኮንትራት ሲያበቃ ወደ አውሮፓ ሊመለስ እንደሚችል የአል ናስር አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሽያ ተናግረዋል።
የቀድሞው የማቸስተር ዩናትድ፣ የሪያል ማድሪድ እና የጁቬንቱስ ኮከብ ሮናልዶ በህዳር ወር በአስቸጋሪ ሁኔታ ከዩናይትድ ጋር ከተለያየ በኋላ በ200 ሚሊዮን ዶላር የሳኡዲውን አል-ናስር ክለብ መቀላቀሉ የሚታወስ ነው።
- የሳኡዲው ክለብ አል ናስር ለሽንፈቱ ፖርቹጋለዊውን ኮከብ ሮናልዶን ተጠያቂ አደረገ
- ክርስቲያኖ ሮናልዶን ከሊዮኔል ሜሲ ያገናኘው የሳዑዲ ጨዋታ በፒ.ኤስ.ጂ አሸናፊነት ተጠናቋል
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊውና 40 ዓመት እስኪሞላው ከአልናስር የሚያቆየው የሁለት ዓመት ውል የተፈራረመው ሮናልዶ ወደ አልናስር ሲመጣ በሳዑዲ አረቢያ ፕሮፌሽናል ሊግ ላይ የራሱን አሻራ ከማኖር በዘለለ የእግር ኳስ ህይወቱ እዚያው እንዲያበቃ ፍለጎት እንዳለው ተናግሮ እንደነበርም አይዘነጋም።
ሮናልዶ ይህን ይበል እንጂ የክለቡ አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሽያ ግን ሮናልዶ ከሳኡዲ በዘለለ በአውሮፓ ምድር ተመልሶ ብቃቱን የሚያሳይበት ሁኔታ ላይ መሆኑ መናገራቸውን ስካይ ሰፖርት ዘግቧል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሳኡዲ አረቢያ ቆይታው በኋላ እንደገና “ወደ አውሮፓ ተመልሶ ይጫወታል” ነው ያሉት አሰልጣኙ።
"ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተከላካዮችን ለመበተን ጉልበት የሚሰጥ አይነት ተጨዋች ነው:: እሱ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ነው። የእግር ኳስ ህይወቱ በአል ናስር አይጨርስም ወደ አውሮፓ ይመለሳል።" ሲሉም አክለዋል ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሽያ።
ሮናልዶ ወደ ማድሪድ ሳይዛወር ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በነበሩት ስኬታማ ዓመታት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች፣ ኤፍኤ ካፕ፣ ሁለት ሊግ ካፕ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫን ማሸነፍ የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው።
በመቀጠልም ከሪያል ማድሪድ ጋር ሁለት የላሊጋ ዋንጫዎችን፣ ሁለት የስፔን ዋንጫዎችን፣ አራት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን እና ሶስት የዓለም ክለቦች ዋንጫዎች እንስቷል።
በጁቬንቱስ በነበረው የሶስት አመታት ቆይታም ሁለት የሴሪ-ኤ እና የኮፓ ኢታሊያ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።
ፐርቹጋላዊው ኮከብ ሮናልዶ ለክለቡ እና ለሀገሩ ከ800 በላይ ጎሎች በማስቀጠር በእግር ኳስ ታሪክ የራሱን ደማቅ ታሪክ የጻፈ መሆኑም በርካቶች የሚስማሙበት ነው።