ኢትዮጵያ አልሸባብ ሊፈጽም የነበረውን የጥቃት ሙከራ ማክሸፏን ገለጸች
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፥ የአልሸባብ ሁለት መኪናዎች እና ስድስት አሸባሪዎች ከነ ፈንጅዎቻቸው ዶግ አመድ ሆነዋል ብሏል

አልሸባብ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ያደረገው በኢትዮጵያ ሶማሊያ ደንበር ዶሎ ካምባስ በተባለ ቦታ ነው
ኢትዮጵያ አልሸባብ ሊፈጽም የነበረውን የጥቃት ሙከራ ማክሸፏን ገለጸች።
ቡድኑ በድንበር ከተማዋ ዶሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወታደሮች ካምፕ ፈንጂ በተጠመደባቸው ሁለት ተሽከርካሪዎች የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ለማድረስ ሞክሯል።
የመጀመሪያው ተሽከርካሪ በወታደሮች ካምፕ መግቢያ ላይ ፈንድቶ አራት ወታደሮችን ማቁሰሉና የንብረት ውድመት ማስከተሉን አናዶሉ የሶማሊያ መንግስት የዜና ወኪል ሶናን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሁለተኛው ተሽከርካሪ ደግሞ ወደ ወታደራዊ ካምፑ ሳይደርስ በኢትዮጵያ ወታደሮች የጥቃት ሙከራው መክሸፉን ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ፥ አልሸባብ በሶማሊያ ዶሎ ከተማ ሊፈጽመው የነበረው የሽብር ተግባር በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መክሸፉን ማሳወቁ ይታወሳል።
የሽብር የቡድኑ አባላት ይዘውት ከመጡት መሳሪያ ጋር መደምሰሳቸውንም ነው የገለጸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ጥቃት ሙከራው ደረሰ ስለተባለው ጉዳት በመግለጫው አልጠቀሰም።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በዛሬው እለት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫም የቡድኑ የአጥፍቶ መጥፋት የጥፋት ሴራ ሙሉ ለሙሉ መክሸፉን ነው ያስታወቀው።
“በኢትዮጵያና ሶማሊያ ደንበር ዶሎ ካምባስ በተባለ ቦታ በአንድ አይሱዚ እና በአንድ ኮብራ መኪና ሙሉ ፀረ ሰውና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጆዎችን ጭኖ በሠራዊታችን ላይ ጉዳት ለማድረስ ቢሞክርም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሁለት መኪናዎች እና ስድስት አሸባሪዎች ከነ ፈንጅዎቻቸው ጋር ዶግ አመድ ሆነዋል” ነው ያለው መግለጫው።
ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግስት በአልሸባብ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ለማገዝና ሽብርተኞች ድንበሯን ዘልቀው እንዳይገቡ ለማድረግ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መላኳ ይታወቃል።
ባለፈው አመት በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ታጣቂዎች ድንበሯን ጥሰው ገብተው ጦርነት ከተካሄደ በኋላም በሶማሊያ ጌዶ ክልል ወታደሮቿን ማስፈሯ የሚታወስ ነው።
ባለፈው ሚያዚያ ወርም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አልሸባብን ለመዋጋት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ እንደሚልኩ መገለጹ አይዘነጋም።
የሽብር ቡድኑ ኢጥዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ ምድር የሚዋጉት ሀገራት ላይ በተለያየ ጊዜ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲሞክር ይታያል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ መሃሙድ በነሃሴ ወር 2022 በአልሸባብ ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ካወጁ በኋላ ቡድኑ በርካታ ይዞታዎችን ማጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
aXA6IDQ0LjIwMC4xMDEuODQg ejasoft island