አሜሪካ ታይሪን ለጠቆመኝ 5 ሚሊየን ዶላር ጉርሻ አሰጣለሁ ብላለች
አሊ ማህሙድ ራጊ፥ በቅጽል ስሙ አሊ ታይሪ ይበልጥ ይታወቃል።
በሞቃዲሾ በፈረንጆቹ 1966 የተወለደው ታይሪ፥ እጽ በማዘዋወር ሃብት አካብቷል።
በሞቃዲሾ በሚገኘው ግዙፍ ገበያ “ባካራ” ሃይማኖታዊ ትምህርት ሲስጥም ታይቷል ይላል የሶማሊያ መንግስት የደህንነት መረጃ።
በብሪታንያ እና ስዊድንም ጽንፈኛ አስተምህሮት ሲዘራ የቆየና በሶማሊያ የአይ ኤስ መሪ የነበረ መሆኑ ነው የሚነገረው።
ስለግለሰቡ ብዙም የሚታወቅ መረጃ ባይኖርም፥ የአልሸባብ ቡድን ዋነኛ የፋይናንስ አንቀሳቃሽና ከቡድኑ አባላት ከፍተኛ ሃብት ያከበተ መሆኑን ነው የደህንነት መረጃዎች የሚያሳዩት።
ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ የአልሸባብ ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለገለው አሊ ታይሪ፥ በአልሸባብ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።
ከበርካታ የሽብር ድርጅቶች መሪዎች ጋር የመሰረትው ግንኙነት እና በእጽ ዝውውር ያካበተው ሃብትም ለተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
አሊ ታይሪ በሶማሊያ እና ኬንያ አልሸባብ በፈጸማቸው በርካት ጥቃቶች በመሳተፍም ተጠያቂ ይደረጋል።
በነሃሴ ወር 2021ም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአለም አቀፍ ሽብርተኛ የፈረጀው ሲሆን፥ ንብረቶቹ እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱ የሚታወስ ነው።
ዋሽንግተን ግለሰቡ ያለበትን ለሚያውቅ ወይንም ዝርዝር መረጃ ለሚሰጥ አካል የ5 ሚሊየን ዶላር ጉርሻ ማዘጋጀቷንም ገልጻ ነበር።
ባለፈው አመት ደግሞ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ማዕቀብ የጣለበት ሲሆን፥ የእንቅስቃሴ እና ሌሎች ገደቦችን መጣሉ አይዘነጋም።
አልሸባብ ይህን ታዋቂ የእጽ አዘዋዋሪና ባለጸጋ ቀጣዩ መሪው አድርጎ ሊሾመው አጭቶታል መባሉን የሶማሊያ የደህንነት መረጃዎች ያመላክታሉ።
አሊ ታይሪ ከፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ ጋር ፊት ለፊት ለመደራደር የውጭ ሀይላት (አሜሪካ) ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣት እንዳለባቸው ማሳሰቡ ተገልጿል።