አልሸባብ ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎቹ እያፈገፈገ ነው ተባለ
አልሸባብ ከወሳኝ ወታደራዊ ይዞታዎቹ ለማስለቀቅ በተካሄደው ዘመቻ ከ2 ሺህ በላይ የቡድኑ አባላት ተገድሏል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በሽብር ቡድኑ ላይ “አጠቃላይ ጦርነት” ማወጃቸው አይዘነጋም
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ነሃሴ 2022 በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ በርካታ ጥቃቶችን በማድረስ የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፈ በሚገኘው አልሸባብ የሽብር ቡድን ላይ “አጠቃላይ ጦርነት” እንደሚካሄድ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
የፕሬዝዳንቱ የጦርነት አዋጅ የመጣው በማዕከላዊ ሶማሊያ የሚገኙ የአካባቢው ጎሳዎች አልሸባብ በግዛታቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በመቃወም ማመጻቸውን ተከትሎ ነበር።
የሶማሊያ መንግስት ወታደራዊ ሃይሎች ከሃምሌ ወር ጀምሮ መጠነ ሰፊ የማጥቃት እርምጃ ሲወስዱ መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው።
ጥቃቱን ተክትሎም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንደለው የሚነገርለትና የቀጠናው ስጋት የሆነው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ፤ ከዋና ዋና ወታደራዊ ይዞታዎቹ እያፈገፈገ ነው ተብሏል።
የሶማሊያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል አዛዥ ኢስማኢል ዳሂር ኦስማን፤ መንግስት ከእነሱ ጋር የሚዋጉትን የአካባቢውን የጎሳ ሚሊሻዎችን መደገፍ ከጀመረ በኋላ አልሸባብ እያፈገፈገ ነው ብለዋል።
"በአልሻባብ ጭቆና ከተማረሩ ከአካባቢው ዜጎች ጋር በመተባበር መንግስት ጥቃት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አልሸባብ በማዕከላዊ ሶማሊያ የነበሩትን ምሽጎቹን እያጣ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የኢስማኢል ዳሂር ኦስማን ሃሳብ እንደሚጋሩ የገለጹት የሶማሊያ የቀድሞ የስለላ ባለስልጣን ኮሎኔል አብዱላሂ አሊ ማው በበኩላቸው ታጣቂዎቹ የቁልቁለት ጉዞ ላይ ናቸው ብለዋል።
አልሸባብ ሲቆጣጠራቸው ከነበሩ ዋና ዋና ከተሞች እና መንደሮች ማፈግፈጉ "የመጨረሻቸው መጀመሪያ ይመስለኛል" ሲሉም ነው የተናገሩት የቀድሞ የስለላ ባለስልጣኑ።
በማዕከላዊ ሶማሊያ እና ደቡብ ምዕራብ ግዛት የሚገኙ እንደ ሂራን፣ መካከለኛው ሸበሌ፣ ጋልሙድግና የመሳሰሉ አከባቢዎችና ከተሞች አሁን ላይ አልሻባብ ለቆ የወጣባቸው እንደሆኑም ቪኦኤ ዘግቧል።
አልሻባብን ከወሳኝ ወታደራዊ ይዞታዎቹ ለማስለቀቅ በተካሄደው ዘመቻ ከ2 ሺህ በላይ የሽብር ቡድኑ አባላት መገዳለቸውም ነው የተገለጸው።
ከተጀመረ ስምንተኛውን ወር ሊያስቆጥር ቀናት ብቻ የቀሩት የሶማሊያ ወታደሮች ጸረ አልሸባብ ዘመቻ በቀጣይ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች አዲስ የጦር ግንባሮችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።