የሶማሊያ ጦር አልሸባብን ከወሳኝ ወደቡ አስለቀቀ
አልሸባብ በተከፈተበት ዘመቻ የባህር ላይ ዝርፊያ ለመፈጸም ከሚጠቀምባት ሃራርድሄር ወደብ ለመልቀቅ ተገዷል ብሏል የሶማሊያ ጦር
ከወደቧ ባሻገር በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ ክልል የምትገኘውን ካልሴድ ከተማም ከአልሸባብ ታጣቂዎች ነጻ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል
የሶማሊያ መንግስት ጦር እና ደጋፊ ታጣቂዎች በጥምረት በአልሸባብ ላይ በከፈቱት ዘመቻ ቡድኑን ከፍተኛ ፋይዳ ካላት ወደብ ማስለቀቅ መቻሉ ተነገረ።
አልሸባብ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የባህር ላይ ዝርፊያ ከፈጸመ በኋላ የሚመሽግባት ሃራርድሄር ወደብ ናት በሶማሊያ ጦር በቁጥጥር ስር የዋለችው።
ከወደቧ ባሻገር በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ ክልል የምትገኘውን ካልሴድ ከተማ ከአልሸባብ ታጣቂዎች ነጻ ማድረግ መቻሉን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከዲር ሞሃመድ ኑር ተናግረዋል።
የተመዘገበው ድል “አልሸባብ አቅሙ መዳከሙንና መጨረሻው መቃረቡን ያሳያል” ብለዋል ሚኒስትሩ።
በትናንትናው እለትም በጥምር ጦሩ በፑንትላንድ ክልል የምትገኘው ኤድሃሪ ከተማን ከአልሸባብ ማስለቀቅ መቻሉን ሬውተርስ ዘግቧል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ግን ስለወደቡም ሆነ ከተሞቹ በመንግስት ሃይሎች መያዝ አስተያየት አልሰጠም።
ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአልሸባብ ላይ የከፈቱት ዘመቻ ውጤት እያስገኘላቸው ነው።
በተለይ በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ቡድኑን ጠራርጎ ማስወጣት መቻሉ አልሸባብ ጣረ ሞት ላይ ይገኛል አስብሏል።
ተንታኞች ግን ቡድኑ ዳግም ራሱን አደራጅቶ ከመመለሱ በፊት አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ከባለፈው አመት ነሃሴ ወር ወዲህ ለተጀመረው ዘመቻ ስኬት የየአካባቢው የጎሳ ታጣቂዎች ድርሻ ትልቅ ነው የሚሉ ባለሙያዎችም ታጣቂዎቹን ይበልጥ የማደራጀትና የመደገፍ ስራ እንዲተኮርበት ነው የሚመክሩት።
ከአልሸባብ ጋር ለአመታት የተካሄደው ጦርነት በሶማሊያ ከፍተኛ የምግብ ችግርን አስከትሏል።
ከ200 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን እጅግ ከባድ በሆነ የምግብ እጥረት ውስጥ ናቸው፤ በርካቶችም በረሃብ እየሞቱ ነው።
ለረሃብ የሚጋለጡት ዜጎች ቁጥር በቀጣዩ አመት ወደ 700 ሺህ ከፍ እንደሚልም የመንግስታቱ ድርጅት ያሳያል።