ሶማሊያ በኤርትራ ሲሰለጥኑ የቆዩትን ወታደሮቿን ማስመለስ ጀመረች
ወታደሮቹ ወደ ኤርትራ የተላኩት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ አስተዳደር ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም
ከኤርትራ የተመለሱት ሶማሊያውያን ወታደሮች "በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ጦርነት ላይ ይሳተፋሉ" ተብሏል
ሶማሊያ ለስልጠና በሚል ምክንያት ወደ ኤርትራ የላከቻቸው ወታደሮቿን ማስመለስ ጀመረች፡፡
መጀመሪያ በኳታር ስራ አለ በሚል የተመዘገቡት ሶማሊያውያን ወጣቶች ለውትድርና ስልጠና ወደ ኤርትራ የተላኩት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ አስተዳደር ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ ለስልጠን በሚል ወደ ኤርትራ የተላኩትን የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ በርካታ ሶማሊውያን እናቶች ያስጨነቀ አጀንዳ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሶማሊያም ሆነች ኤርትራ ለረዥም ጊዜ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው ነበር።
ነገርግን በቅርቡ ከስልጣን የተሰናበቱት የቀድሞ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ባስረከቡበት ወቅት 5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ምድር ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በግንቦት ወር ወደ ስልጣን የመጡት የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያውያን ወታደሮች ወደ ሀገራቸው እንደሚመልሱ ቃል ገብተው ነበር፡፡
እናም በኤርትራ ሲሰለጥን የቆየው የመጀመሪያው የሶማሊያ ወታደሮች ቡዱን አሁን ላይ ወደ ሀገሩ መመለስ መጀመሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር መሀመድ ኑር ፤ ከኤርትራ የመጡት የመጀመሪያ ምድብ ወታደሮች ረቡዕ እለት ሶማሊያ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስተሩ ወደ ሀገራቸው ስለተመለሱትን ወታደሮች ብዛት ግን የገለጹት ነገር የለም፡፡
ከኤርትራ የተመሰሉት ሶማሊያውያን ወታደሮች "በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ጦርነት ላይ ይሳተፋሉ" ም ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ፡፡
በኤርትራ የሚገኙትን ሶማሊያውያን ወታደሮች ወደ ሀገራቸው መመለስ ሼህ ማህሙድ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከገቡት ቃል ውስጥ አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡