ጄነራል መሃመድ የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከነበሩ ጦር አዝማች ጄነራሎች መካከል ናቸው
አልሸባብ ትናንት ሞቃዲሾ በሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት የቀድሞውን የሶማሊያ ጦር ጄነራል መሃመድ ኑር ገላልን ገደለ፡፡
ጄነራል መሃመድ የዚያድ ባሬ ጦር በ1969/70 ዓ/ም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከነበሩ ጦር አዝማች ጄነራሎች መካከል ናቸው፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር እና የሶማሊያ ጦር መሪ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
“የኦጋዴን ጦር መሃንዲስ” ተደርገው ነው በብዙሃኑ ሶማሊያውያን ዘንድ የሚታወቁት፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ጦርነቱን በድል ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው፡፡ የካራማራ ድል የተመዘገበበት 43ኛ ዓመትም የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ልክ እንደቀደመው ዓመት ሁሉ በድምቀት ይከበራል፡፡
ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በጄነራሉ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
ጄነራል መሃመድ ብቃት ያለውን ብሄራዊ ጦር ለማደራጀት በሰሩት ስራ ሲታወሱ እንደሚኖሩም ነው ፕሬዝዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
መሃል ሞቃዲሾ በሚገኘው አፍሪካ ሆቴል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ጄነራሉን ጨምሮ 9 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ጥቃቱ ጄነራሉ አባል የሆኑበት የሃዊዬ ጎሳ አመራር አባላት በሆቴሉ ተሰብስበው በመጪው ምርጫ የውክልና ጉዳይ ላይ በመምከር ባሉበት ሁኔታ ላይ የተፈጸመ ነው፡፡
አልሸባብ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ፡፡
“ሙጃሂዲኖቼ የክህደት አባላቱ የተሰባበሰቡበትን ሆቴል በተኩስ አናወጡት” ሲልም ነው መግለጫ ያወጣው፡፡
አክራሪው ቡድን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የሶማሊያ መንግስት በመገልበጥ የራሱን ሃይማታዊ መንግስት ለመመስረት የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡
ሆኖም እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የጸረ ሽብር ጦር ተገትቶ ሞቃዲሾን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡