ብሄራዊ በዓል ሆኖ በየዓመቱ እንዲከበር ይሰራል
ብሄራዊ በዓል ሆኖ በየዓመቱ እንዲከበር ይሰራል
ብዙዎች ተዘንግቶ ስለመቆየቱ የሚናገሩለት 42ኛው የካራማራ ድል የመታሰቢያ በዓል ዛሬ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት ፓርክ ተከብሯል፡፡
በስነስርዓቱ በጦርነቱ በመሳተፍ ብቻም ሳይሆን በፈጸሙት ጀብድ የሚጠቀሱ የቀድሞው ጦር ሰራዊት አባላት የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ማህበር አመራርና አባላት እንዲሁም በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ እና የኤምባሲው ባልደረቦችም የበዓሉ ታዳሚያን ነበሩ፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋም በመታሰቢያ በዓሉ ተገኝቷል፡፡
የድሉን ታላቅነት ያነሱት የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበበ አያሌው የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት በደም የተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡
ማህበሩም ይህን ወዳጅነት መሰረት አድርጎ የተመሰረተ ነው ያሉም ሲሆን አባላቱ ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ በኩባ ሪፐብሊክ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ተምረው ህብረተሰባቸውን በማገልገል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓሉ ብሄራዊ በዓል ሆኖ በየዓመቱ እንዲከበር ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የህ/ሰብ ክፍሎች ማህበራትና የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ሲሉም ነው ቃል የገቡት፡፡
በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ቀኑን ታሪካዊ ብለውታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከኩባ ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን ከ42 ዓመታት በፊት የሃገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር መዋደቃቸው በሚታሰብበት በዚህ እለት እንድናገር መፈቀዱ ለእኔ ክብር ነው ያሉት ድሉ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ድሉን በምንዘክርበት ወቅት ኩባ ወታደር ብቻ ወደ አለመላኳን መናገሩ አስፈላጊ ነው ያሉም ሲሆን በህክምናና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ 41 ሺ 730 ኩባውያን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ማገልገላቸውን ገልጸዋል 173ቱ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ መክፈላቸውን በመጠቆም፡፡
”በኢትዮጵያ ያገለገሉ ኩባውያን ወታደሮች ወደ ሃገራቸው ይዘው የሄዱትም ሆነ ያፈሩት ሃብት የለም ፤ ለመስዋዕትነታቸው የጠየቁት ክፍያም አልነበረም፤ ከጓዶቻቸው አጽምና ከዘላቂው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናና ወዳጅነት በስተቀር“ ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
የሃገርን ዳር ድንበር የደፈረውን ወራሪ ጠላት ለመመከት በተካሄደው በዚህ ጦርነት የተሳተፉ ጀግኖችም የጦርነቱን ሁኔታ ሊያስቃኝ የሚችል ንግግርን አድርገዋል፡፡
ወጣት ሳሉ በጦርነቱ መሳተፋቸውን የተናገሩት የቀድሞው ወለጋ ክፍለሃገር ቤጊ ተወላጅ ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ የሚወደሱበትን የጀብደኝነት ታሪክና እንዴት ባለመልኩ የጠላትን ታንኮች በቦምብ እንዳጋዩ ለታዳሚው ገልጸዋል፡፡
አዳኝ መሆናቸው በጦርነቱ ጀብድን ለመፈጸም እንዳገዛቸው የገለጹት ሻለቃ አሊ ጥይት ሳይባክን የተጣለባቸውን ግዳጅ እንዴት ይወጡ እንደነበረም አስቃኝተዋል፡፡
አሊ በርኪ በፈጸሙት ጀብድ ትልቁን የሃገሪቱን ኒሻን በደርግ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም እስከመሸለም ደርሰዋል፡፡
ሆኖም ከድሉ በኋላ ሽልማቱን እስከ መነጠቅና ለእስር እስከመዳረግ የደረሰ እንግልት እንደደረሰባቸውና ጎስቋላ ህይወት ለመመራት ስለመገደዳቸው በስነ ስርዓቱ ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያው ውጊያ ነሃሴ 24 ቶጎጫሌ አቅራቢያ መካሄዱን የገለጹት የቀድሞው ጦር አመራር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ በበኩላቸው ሊነገር የሚገባው የድል ታሪክ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሊመሰገን ይገባዋል ያሉት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ የሚያስችል አኩሪ ገድል መፈጸሙንም ነው ገለጹት፡፡
የካራማራ ጀግኖች ወጣት ሳሉ ገድል መፈጸማቸውን በመሰከረ አንደበታቸውም ”ታሪካችሁን አንብቡ እወቁ ታሪክ ስሩ ከኢትዮጵያም ውጭ ሃገር የላችሁም “ ለታዳሚው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ድባቅ የተመታበትን የካራማራ ድል ለመዘከር በተዘጋጀው በዚህ ስነ ስርዓት ሰማዕታቱን የሚያስታውስ የአበባ ጉንጉን ተቀምጧል፡፡
ድሉ የካቲት 26 1970 ዓ/ም መመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡