የአውሮፓ ህብረት በሶማሊያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለማጠናከር 116 ሚሊዮን ዶላር አጸደቀ
አልሸባብ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተሰዘነረበት ባለው ጥቃት ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎቹ እያፈገፈገ መሆኑ ይነገራል
ድጋፉ በአብዛኛው በሶማሊያ ለማረጋጋት ለሚሰማሩ የአፍሪካ ወታደሮች በአበል መልክ የሚሰጥ ነው ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት በሶማሊያ የቀጠናው ስጋት የሆነውን አልሸባብ ለማዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ወደ 116.6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈቅዷል።
ድጋፉ በ2023 ለአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) እና ለሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ከተሰበሰበው 26.6 ሚሊየን ዶላር አጠቃላይ የፋይናንስ አቅም የ90 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ያለው መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ ድጋፉ የጸጥታ ሃላፊነቶችን ከአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ለሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ለማስረከብ የሚደረገውን ሂደት አስተማማኝ ለመድረግና በቀጣይ ሀገሪቱን የማረጋጋት ግዳጅ የሚወጣውን የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ዝግጁ ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል፡፡
በዚህም መሰረት ድጋፉ በአብዛኛው በሶማሊያ ለማረጋጋት ለሚሰማሩ የአፍሪካ ወታደሮች በአበል መልክ እንደሚሰጥና ለሶማሊያ ጦር የሚሰጠው ገንዘብ ለመሳሪያዎች አቅርቦት እና በመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ እንደሚውል ተጠቁመዋል፡፡
የአልቃይዳ ዋነኛ አጋር እንደሆነ የሚነገርለት አልሸባብ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተሰዘነረበት ባለው ጥቃት ኩፉኛ እየተዳከመና ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎቹ እያፈገፈገ መሆኑ ይነገራል፡፡
የሶማሊያ የቀድሞ የስለላ ባለስልጣን ኮሎኔል አብዱላሂ አሊ ማው በቅርቡ የአልሸባብ ታጣቂዎች " ጣቂዎቹ የቁልቁለት ጉዞ ላይ ናቸው " ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
አልሸባብ ከበርካታ ይዞታዎች ማፈግፈጉ "የመጨረሻቸው መጀመሪያ ይመስለኛል" ሲሉም ነው የተናገሩት የቀድሞ የስለላ ባለስልጣኑ።
ላለፉት ስምንት ወራት የተካሄድትን ዘመቻዎች ተከትሎ አሁን ላይ አልሸባብ ቀደም ሲል ይዞዋቸው ከነበሩ ማዕከላዊ ሶማሊያ እና ደቡብ ምዕራብ ግዛት የሚገኙ እንደ ሂራን፣ መካከለኛው ሸበሌ እና ጋልሙድግ የመሳሰሉ አከባቢዎችና ከተሞች ለቆ መውጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡