ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአፋጣኝ እንደሚለዩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል
ወሎ ዩኒቨርስቲ በኪራይ አውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እያደረገ ነው
የግብርና ሚኒስቴር ከኬንያ በኪራይ ባመጣው አውሮፕላን በወሎ አንበጣ በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የጸረ-አንበጣ ኬሚካል ርጭት መደረጉን እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኬንያ የመጡ ባለሙያዎችን በመደገፍ የማስተባበር ስራ መስራቱን ዩኒቨርሲቲው ገለጸ።
ዩኒቨርስቲው በአንበጣ መንጋው ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር አፋጣኝ ቀጥተኛ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ በቦርድ አመራሩ መወሰኑንም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
መንጋው ከተከሰተበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከወልዲያ እና ሠመራ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ሁኔታውን ስናጠናና ስንከታተል ነበር ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ተማሪዎችን በማስተባበር ሰብል ሲሰበስቡ እንደነበረም ነው የገለጹት፡፡
የወሎ ዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር)
አሁንም አንበጣውን ለመከላከል ከኬንያ በመጡ ባለሙያዎች በመታገዝ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
"አውሮፕላኑ በሰሜን ወሎ በወረባቡ እና ሌሎችም አካባቢዎች በቀን 6 ጊዜ እየተመላለሰ ላለፉት 10 ቀናት ርጭት አድርጓል” ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይም ከየአካባቢው የመንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት የመከላከል ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉም ሲሆን ከእለት እለት እየሰፋ የመጣውን የአደጋውን ሁኔታ በመገምገም ተጎጂዎች ተለይተው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ለዚህም የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም አባል የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ዝግጁነት አላቸው ያሉት የፎረሙ ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ በተናበበ እና በተቀናጀ መንገድ ድጋፎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
መንጋው ሊሰበሰብ ከተቃረበው ሰብል ባሻር በእንስሳት መኖ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት የዩኒቨርስቲው ቦርድ አባል ብርሃኑ አድማሱ (ዶ/ር) ህብረተሰቡን ከሚደርስበት ስነ ልቦናዊ ጫና ለመታደግ እና መኖ ለማቅረብም ጭምር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው ለአደጋው በእውቀት የታገዘ ምላሽን ለመስጠት እንዲችል ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የገለጹት የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) "ቀጥተኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአፋጣኝ ይለያሉ” ብለዋል።
"መንግስት ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም መባሉ ተገቢ አይደለም” ያሉት ሚኒስትሯ በአካባቢው 13 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ነው የገለፁት።
ሁሉም አካላት የተቀናጀ ድጋፍን እንዲያደርጉም ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በትዊተር ገጻቸው ሁለት አውሮፕላኖች መግባታቸውን እና ሶስተኛው ደግሞ ዛሬ ገብቶ ወደ ኮምቦልቻ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል የሚረጩ 5 አውሮፕላኖችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ከውጭ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ከትናንት በስትያ ጥቅምት 01 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡