የተለያዩ የምግብ እና የመድኃኒት ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል እየተጓጓዙ ነው
የዕለት ደራሽ የምግብ እርዳታዎችን የጫኑ በርከት ያሉ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቀሌን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ደርሰዋል ተብሏል
ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶባቸዋል የተባለላቸው የመድኃኒት ቁሳቁሶች ወደ መቀሌ፣ አዲግራትና ሽሬ ከተሞች በመጓጓዝ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል እያተጓጓዘ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶቹ ከትናንት ጀምሮ ወደ መቀሌ፣ አዲግራትና ሽሬ ከተሞች በመጓጓዝ ላይ ነው ናቸው ያለው ኤጀንሲው ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶባቸዋል ያለ ሲሆን ከነገ ጀምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ይሰራጫሉ ብሏል።
በመጓጓዝ ላይ ካሉት መድኃኒቶች መካከል ድንገተኛ ለኩላሊትና ለስኳር ሕሙማን እንዲሁም ለእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ይገኙበታል።
ለምዕራብና ደቡባዊ ትግራይ ዞኖች በኤጀንሲው የአማራና የአፋር ክልል ቅርንጫፎች በኩል መድኃኒቶች እንደሚሰራጩም አስታውቋል።
12,500 ኩንታል የምግብ አቅርቦት እና ተጨማሪ 7000 ኩንታል የስንዴ ዱቄት የጫኑ ከ30 በላይ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ መላካቸውን ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ወደ ሽሬ፣ አላማጣ እና ሌሎች አካባቢዎችም ድጋፎች መላካቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መቀጠሉን የገለጸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ ቤት አሁን ላይ ደግሞ ለክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ድጋፍ ማድረስ ተጀምሯል ብሏል፡፡
ከህዳር ወር ጀምሮ የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የመጀመሪያ ዙር የሰብአዊ ዕርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ዳንሻ ፣ ወደ ወልቃይት ፣ ወደ ቃፍታ / ሁመራ እና ወደ ደባርቅ አካባቢዎች በመንግሥት መላካቸውንም ጽ/ቤቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያቀርበው በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋርም በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ነው ጽ/ቤቱ ያስታወቀው፡፡