አል ቡርሃን የሱዳን ወታደራዊ ክንፉ ስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌለው ገለጹ
ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት ከሃምዶክ እና ከአልቡርሃን ጋር ተገናኝተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሱዳንን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉት ነው ተብሏል
በመፈንቅለ መንግስት ከኃላፊነት ተነስተው በቤት ውስጥ እስር ላይ የሚገኙት የሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከአሜሪካዋ ዲፕሎማት ጋር መገናኘታቸውን የዋሸንግተን ባለስልጣን አስታወቁ፡፡
ከአብደላ ሃምዶክ ጋር የተገናኙት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ማሪ ካትሪን ፒ ናቸው፡፡ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በትዊተር ገጹ እንዳለው አምባሳደር ማሪ ካትሪን ፒ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተዋል፡፡
- የሱዳን ጦር በዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተኮሰው ጥይት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፈ 10 ሰዎች ቆሰሉ
- የሱዳን ሲቪል ጥምረት ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚደረገውን ድርድር ውድቅ አደረገ
ዲፕሎማቷ ከአብደላ ሃምዶክ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ፤ ዋሸንግተን የሱዳን ሽግግር መንግስት ወደ ቦታው ፍላጎት አላት ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ማሪ ካትሪን ፒ ከአብደላ ሃምዶክ በተጨማሪም መፈንቅለ መንግስት ካደረጉት የሱዳን ሉዓላዊው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሀን ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
አልቡርሃን በዋሸንግተን እና ካርቱም መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት አድንቀው ይህንን የበለጠ ለማጠናከር ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ወታደራዊ ክንፉ ስልጣን ላይ መቆየት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሀገርን ወደ መረጋጋት የሚያመጣ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሽግግር ሂደቱ ላይ የውጭ ኃይሎች መግባታቸው ሂደቱን እንዳሰናከለው አብደል ፈታህ አልቡርሃን ለአሜሪካዋ ዲፕሎማት የገለጹላቸው ሲሆን፤ በሱዳን የታሰሩ ሰዎች መፈታታቸውን በቀጣይም ወንጀል የማይገኝባቸው ከእስር እንደሚፈቱም ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡
በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ምርጫ እንዲደረግ እና አሜሪካም ለዚህ ምርጫ እና ሽግግር ድጋፍ እንደምታደርግ አምባሳደር ማሪ ካትሪን ፒ ተናግረዋል፡፡ ምርጫው እና ሽግግሩ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንዲሆን መሰራት እንዳለበትም የገለጹት ዲፕሎማቷ ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሱዳንን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተሉትና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
ሱዳናውያን ችግራቸውን በራሳቸው እንደሚፈቱና የዋሸንግተን አስተዋጽኦ የሚሆነው ሁኔታቸውን ማመቻቸት ብቻ እንደሆነም ዲፕሎማቷ ተናግረዋል፡፡