የሱዳን ሲቪል ጥምረት ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚደረገውን ድርድር ውድቅ አደረገ
ጥምረቱ አልቡርሃን ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት የነበራቸውን የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣን እንደማይቀበል ገልጿል
አል-ቡርሃን እስከሁን የወሰዷቸው እርምጃዎች እንዲቀለብሱ ከዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጫና እየተደረባቸው ነው
የሱዳን ዋናው የሲቪል ፓለቲካዊ ጥምረት ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚያደረገውን ድርድር ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ጥምረቱ በጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሀን ከተመራው የጥቅምት 25 መፈንቅለ መንግስት በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚደረገውን ድርድር ተቃባይነት የለውም” ብሏል፡
መግለጫውን ያነበቡት ቃል አቀባይ አልዋቲክ ኤልቤሬር ፤ እንደፈረንጆቹ በ2019 አምባገነኑ ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሰራዊቱ ጋር የስልጣን ክፍፍል ስምምነት የተፈራረመው ‘የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች’ መፈንቅለ መንግስቱን ውድቅ ማድረጋቸውንና ከወታደሩ ጋር አለመገናኘታቸው ገልጸዋል፡፡
በቤት እስር ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሃመዶክ እንደሚደግፍ የገለጸው ጥምረቱ፤ ሁሉም ነገር ከመፈንቅለ መንግስት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለለስም ጠይቋል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ የተካሄደው ሲቪሎች ባነሷቸው ኋላም ወደ ጠረጴዛ በመጡ ጥያቄዎች እንደነበር ያስታወሱት ሌላኛው የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች ቃል አቀባይ በበኩላቸው “አጋርነቱን አላፈረስንም…ወደ ህገ-መንገስታዊ ሰነዶች መለስ ብለን መመልከት ይኖርብናል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“ መፈንቅለ መንግስቱ የወታደሩ ተቋም አይወክልም”ም ብሏል፡፡
አል-ቡርሃን ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት የነበራቸውን “የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድርነት ስልጣን ጥምረቱ አይቀበልም”ም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ኤልቤሬር በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ በርካታ ሲቪል ፖለቲከኞች እና ባለስልጣናት ወደ ዘብጥያ ወርደው በከባድ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
አል-ቡርሃን በሱዳን ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እውን እንዲሆንና እንደፈረንጆቹ በሃምሌ/2023 የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡አል-ቡርሃን እንዲህ ቢሉም ግን ፡የወሰዱትን እርምጃ እንዲቀለብሱ ከዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጫና እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት የሱዳንን አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ የተመድ ልዩ መልዕክተኛ ቮልከር ፓርተስ የሚያቀርቡለትን ሪፖርት የፊታችን እሁድ ለማድመጥ ቀጠሮ እንደያዘም ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን የሚገኙ“የረዚስተንስ ኮሚቴዎች” ህዳር 13 እና 17 በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወደ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸው እንዲገልጹ የሰልፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኮሚቴዎቹ በሚመሩት የተቃውሞ ሰልፍ ፡ “ምንም ዓይነት ድርድር የለም፣አጋርነት የለም፣ ምንም ቅቡልነት የለም” የሚሉ መፈክሮች የሚደመጡና የሚንጸባረቁ ይሆናሉም ነው የተባለው፡፡
በዳርፉር እና በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች፤ በህዳር 13 በሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚሳተፉ ከወዲሁ አስተውቀዋል፡፡
ኮሚቴዎቹ ምንም እንኳን በኢንተርኔት መቆራረጥ ውስጥ እየታገሉ ቢሆንም፣ በጥቅምት 30 ወታደራዊ ኃይሉን የሚቃወሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የወጡበት ሰልፍ ማስተባበር ችለዋል፡፡ በቀጣይ የስራ ማቆም አድማ እና ህዝባዊ እምቢተኝነት ዘመቻ ሊኖር እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡