የሱዳን ጦር በዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተኮሰው ጥይት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፈ 10 ሰዎች ቆሰሉ
ሱዳን በሀገሪቱ የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ ብዛት ያለው ጦሯን በካርቱም ጎዳናዎች ላይ አሰማርታለች
ተመድ የሱዳን ጦር ወደ ሰልፈኞች ጥይት እንዳይተኩስ አስቀድሞ አሳስቦ ነበር
ሱዳን በሀገሪቱ የተከሰተውን የተቃውሞ ሰልፎች ለማስቆም ብዛት ያለው ጦሯን በካርቱም ጎዳናዎች ላይ አሰማራች።
በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ከሳምንታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚመራው ሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም አመራሩንም ማሰሩ ይታወሳል።
መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድሩ እንዲመልስ የተለያዩ ጫናዎች በመደረግ ላይ ቢሆንም የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረታቸውን ከትናንት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎ ሱዳናዊያን አዲሱን የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ናቸው።
ይሁንና ሰልፉን ለማስቆም ብዛት ያለው የሱዳን ጦር በካርቱም አደባባዮች መሰማራታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የሱዳን መከላከያ ሰራዊት፣ ፖሊስ፣ የሱዳን ተጠባባቂ ሀይል እና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ወደ ካርቱም አደባባዮች እና ድልድዮች በመውጣት መንገድ ዘግተዋል ተብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ የሱዳን ጦር በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት እንዳይተኩስ እና ዜጎችን እንደይጎዳ አስቀድሞ አሳስቧል።
ይሁንና አሁን ላይ በወጣ ዜና የሱዳን ጦር ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ተኩሶ ማቁሰሉን እና አንድ ሰው ደግሞ መግደሉን የሱዳን ሀኪሞች ማህበር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሱዳን ወታደራዊ አመራር የዘጋውን ኢንተርኔት እንዲከፍት በአገሪቱ ፍርድ ቤት የታዘዘ ቢሆንም አሁንም ኢንተርኔት እንደተዘጋ ሲሆን ሱዳናዊያንን በመደበኛ የጽሁፍ መልዕክት በመለዋወጥ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።